ቤዛዊት ታደሰ ወደ እግር ኳስ ለመመለስ ድጋፍ ትሻለች

ወጣቷ አጥቂ ቤዛዊት ታደሰ በጉልበቷ ላይ በደረሰ ጉዳት ከሜዳ ከራቀች ሦስት ወራት ያለፋት ሲሆን ወደ ሜዳ ለመመለስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፃለች፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተስፋ ከተጣለባቸው ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዷ የሆነችው ፈጣኗ የአጥቂ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ቤዛዊት ታደሰ በ2009 ክረምት ደቡብ ክልልን ወክላ በመላው ኢትዮጵያ ውድድር ስትጫወት ባሳየችው እንቅሴቃሴ በዛኑ ዓመት በደደቢት የመጫወት ዕድልን አግኝታ እስከ 2010 መቆየት ችላለች። በ2011 የውድድር ዘመን አዲስ አበባ ከተማ በመጫወት ያሳለፈችው ተጫዋቿ የመዲናይቱን ክለብ በክረምቱ የዝውውር ወቅት ወደ ጌዲኦ ዲላ ማምራት ብትችልም በዝግጅት ወቅት ከክለቧ ጋር በልምምድ ላይ ሳለች ከጉልበቷ በታች (ACL) ጉዳት ገጥሟት ከሜዳ ከራቀች ወራቶችን አስቆጥራለች። ተጫዋቿ ህክምና ለማድረግ ያሰበች ቢሆንም “የህክምና ወጪው ከአቅሜ በላይ ነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ወደምወደው እግር ኳስ እንድመለስ ከጎኔ ይቁምልኝ።” ስትል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡

“የተጎዳውት በዝግጅት ላይ እያለው ነው። ከጉልበቴ በታች አሸማቀቀኝ፤ በሂደት ግን ልምምድ እየሰራሁ እየዳንኩ መስሎኝ ነበር። ሆኖም እየባሰብኝ መጣ፤ ለህክምና ወደ ካዲስኮ ሆስፒታል አምርቼ ሰርጀሪ መሰራት አለብሽ ተብያለሁ። ከ160 ሺህ ብር በላይ ተጠይቄያለሁ። አሁን ቀጠሮ ተይዞልኛል፤ ለመታከም ደግሞ እኔ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ሁሉም ከጎኔ ሆኖ ወደ እግር ኳስ እንዲመልሰኝ እና እንዲረዳኝ በፈጣሪ ስም እማፀናለሁ።” ብላለች። ተጫዋቿ የጌዲኦ ዲላ አዲስ ፈራሚ ብትሆንም “ክለቡ እስካሁን ከጎኔ አይደለም” ስትልም ቅሬታዋን ገልፃለች፡፡

✿ቤዛዊት ታደሰን ለመርዳት

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
– ቤዛዊት ታደሰ ዳኜ
– 1000181220426


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ