የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማኅበር 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው

ጤናማ ስፖርተኛ ማፍራት ዓላማው ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማኅበር 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በተለያዩ ፕሮግራሞች እየተከበረ ይገኛል።

የዛሬ 25 ዓመት ምስረታውን ያደረገው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማኀበር የ25ኛ ዓመት በዓሉን መሠረት ያደረገ የተለያዩ ዝግጅቶችን ከጥር 3 –9 ቀን ድረስ እያከበረ ይገኛል። ዛሬ ከ08:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በርካታ የማኀበሩ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የበዓሉ አንዱ አካል የሆነው ሲንፖዚየም ተካሂዷል።

የማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ ተፈራ ደንበል የመክፈቻ ንግግር በማደረግ በተጀመረው በዚህ መድረክ “የስፖርት ጠቀሜታ” ምን እንደሆነ በአቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ አማካኝነት ጥናታዊ ፁሑፍ ቀርቧል። በጥናታዊ ፁሑፋቸውም ስፖርት ኀብረተሰብና ለማቀራረብ ፣ ጤና ኀብረተስብ ለመፍጠር እና በፖለቲካ የተራራቁ ህዝቦችን ለማቀራረብ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በመግለፅ ይህን ስፖርት ለማስፋፋት ፣ ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ የስፖርት ፅንሠ ሀሳብና ጠቀሜታን ግንዛቤ መፍጠር፣ የስፖርቱን አደረጃጀት እስከ ታች ድረስ ወርዶ መዘርጋት፣ የአሠራር ስርዓቱንም በህጋዊ መንገድ መዘርጋት እና የስፖርት ማዘውተርያ ሥፍራን ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል።

በማስከተል ዶ/ር አያሌው ጥላሁን “የስፖርት እንቅስቃሴ ለጤንነት” በሚል ጥናታዊ ፁሑፍ አቅርበዋል። ስፖርት ለሁሉም ማኀበረሰብ ለጤንነት አስፈላጊ መሆኑ ገና በሀገራችን እንዳልዳበረ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልገው ገልፀው። በዚህም ምክንያት ትንሽ ትልቁ ለተለያዩ በሽታዎች በመጋለጥ ጤንነት የጠፋው በስፖርት የዳበረ አካል መፍጠር ባለመቻሉ ነው። ከአካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረጉ እንዳለ ሆኖ ከዚህ ባሻገር ከአመጋገብ፣ ከምንጠቀምባቸው መጠጦች እና ከአኗኗራችን ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጤና እንከኖች በሀገራችን ተበራክተዋል ያሉት ዶ/ር አያሌው ለዚህም መፍትሔው ከበሽታ የነፃ፣ ሰውነቱን የተረዳና የሚቆጣጠር፣ ከመድሐኒቶች የነፃ፣ ከዓለም ጋር የሚጓዝ፣ ሩቅና ጥልቅ አሳቢ እና ፍላጎቱን የለየ ዜጋ ለመሆን ያሰበ ሰው የስፖርት እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው በማለት ፈገግ እያደረጉ በጨዋታ የተዋዛ ጠቀሜታ ያለው ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በመቀጠል የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማኅበርን የ25 ዓመት ጉዞ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል። በመጨረሻም ነገ ቅዳሜ ከ ጥር 9 ቀን ቄራ በሚገኘው አልማዝዬ ሜዳ ከጠዋቱ 02:00 ጀምሮ በሚከናውን የእግርኳስ ውድሮች የመዝጊያ ፕሮግራም የበዓሉ ፍፃሜ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ