ተስፋዬ አለባቸው ከነገው የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ውጭ ሆኗል

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የሲሸልሱን ሴንት ሚሼል ዩናይትድ ነገ የሚገጥመው ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸውን በጉዳት አጥቷል፡፡

ጠንካራው አማካይ ሀሙስ እለት ቡድኑ ባደረገው ልምምድ ላይ ከቢያድግልኝ ኤልያስ ጋር ተጋጭቶ ቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ተስፋዬ ትላንት በተደረገው ልምምድ ላይ ቀለል ያለ ልምምድ ማድረግ ቢችልም ከጉዳቱ ማገገም አልቻለም፡፡ በዛሬው ልምምድ ላይ ከቡድኑ ጋር ቢገኝም ተቀምጦ በመመልከት አሳልፏል፡፡ በዚህም ምክንያት የነገውን ጨዋታ ካደረገ ጉዳቱ ሊባባስ ስለሚችል ጨዋታውን እንዳያደርግ በሀኪሞች ተወስኗል፡፡

ነገ ሴንት ሚሼልን ከሚገጥመው ቡድን ውስጥ ቋሚ ተሰላፊዎቹ ተስፋዬ አለባቸው እና ብሪያን ኡሞኒ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ ያለፉትን ሁለት ልምምዶች ያልሰራው የመስመር አጥቂው ዳዋ ሁቴሳም የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል ተብሏል፡፡ በራስ ምታት ህመም ምክንያት አንድ ቀን ልምምድ ያልሰራው ሮበርት ኦዶንካራ ዛሬ ወደ ልምምድ ተመልሷል፡፡

ያጋሩ