ሪፖርት | ውጥረት የበዛበት ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ለ12 ደቂቃዎች ያክል የተቋረጠው የባህር ዳር ከተማ እና የወልዋሎ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ሀዋሳ አምርተው በሲዳማ ቡና 3-1 ከተረቱበት የመጀመርያ 11 ደረጄ መንግስቱ እና ፍቃዱ ወርቁን በፍፁም ዓለሙ እና ዜናው ፈረደ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል። ተጋባዦቹ ወልዋሎዎች ደግሞ በሜዳቸው በሀዲያ ሆሳዕና አንድ ለምንም ከተሸነፉበት ጨዋታ ጃፋር ደሊል፣ ራምኬል ሎክ እና ሰመረ ሃፍተይን በዓብዱላዚዝ ኬይታ፣ ብሩክ ሰሙ እና አሞስ አቼምፖንግ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የባህር ዳር ከተማ ደጋፊ ጌታቸው ፈንቴ የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል። በጨዋታው ጅማሮ ላይ ሁለቱ ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን በማብዛት ወደየተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ሞክረዋል። ቡድኖቹ በተለይ ከመስመር በሚነሱ እና ከቆሙ ኳሶች ጥቃቶችን በመሰንዘር ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴን ተጋባዦቹ ወልዋሎዎች በ8ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ በአሞስ አቼምፖንግ አማካኝነት ወደ ግብ ቀርበው መክኖባቸዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የቅጣት ምት ያገኙት ባለሜዳዎቹ በራሳቸው በኩል የተገኘን የመጀመሪያ ሙከራ ወደ ግብነት ቀይረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ማማዱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግምባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል።


በእንቅስቃሴ ደረጃ የተቀዛቀዘ የጨዋታ ጅማሮ እያስመለከተ የቀጠለው ጨዋታው በ25ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል አስተናግዷል። በራሱ የግብ ክልል ኳስ ሲገፋ የነበረውን ዜናው ፈረደን የቀሙት ወልዋሎዎች ኳሷን በቶሎ ወደ መስመር በማውጣት ያገኙትን አጋጣሚ በኢታሙና ኬሙይኔ አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረው አቻ ሆነዋል። ከዚህች ግብ በኋላ እየተነቃቃ የመጣው ጨዋታው በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ማስተናገድ ጀምሯል።

በ25ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ ያስቆጠሩት ቢጫ ለባሾቹ ከ2 ደቂቃ በኋላ ብሩክ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ በግምባሩ በመግጨት በሞከረው ኳስ መሪ ለመሆን ጥረዋል። የብሩክን የግንባር ኳስ በቀላሉ የተቆጣጠረው ሃሪስተን ሄሱ ኳሱን በረጅሙ ለማማዱ ሲዲቤ አሻግሮለት ማማዱ ጥሩ ሙከራ ሰንዝሯል።


ጥቃቶችን ከየአቅጣጫው መሰንዘር የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ31ኛው ደቂቃ ዜናው ከፍፁም የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂ ጃፋር ደሊል እንደምንም አውጥቶበታል። ከ2 ደቂቃዎች በኋላ በመስመር ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግርማ ዲሳሳ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ ጃፋር መረብ ላይ አርፎ ባህር ዳሮች ዳግም መሪ ሆነዋል። ይህ ግብ የበቃቸው የማይመስሉት ባህር ዳሮች በ33 እና በ35ኛው ደቂቃ ማማዱ በእግር እና በግምባር በሞከራቸው ጥሩ ጥሩ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል።

የመልሶ ማጥቃት እድሎችን በመጠቀም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥሩ የነበሩት ወልዋሎዎች በ38ኛው ዲቂቃ ሚካኤል ለማ ከርቀት ወደ ግብ በመታው ኳስ ዳግም በጨዋታው አቻ ለመሆን ጥረዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው አሞስ አቺምፖንግ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ እጅግ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በባለሜዳዎቹ መሪነት ተጠናቋል።


በመጀመሪያው አጋማሽ የሚፈልጉትን ያገኙት ባለ ሜዳዎቹ በዚህኛው አጋማሽ ተዳክመው ታይተዋል። በአንፃራዊነት በመጀመሪያው አጋማሽ ተቆጥበው ሲጫወቱ የነበሩት ወልዋሎዎች እጅግ ተጠናክረው ወደ ሜዳ በመግባት ጥቃቶችን መሰንዘር ጀምረዋል። አጋማሹ በተመጀረ በ46ኛው ደቂቃም ወልዋሎዎች ሚካኤል ከመስመር ባሻማው ነገር ግን ብሩክ ባልተጠቀመበት ጥሩ አጋጣሚ አጀማመራቸውን ለማሳመር ጥረዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ጁኒያስ ናንጂቡ ከመሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የባህር ዳር ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውበታል። የባህር ዳር መቀዛቀዝ የጠቀማቸው የአሰልጣን ዮሐንስ ሳህሌ ተጨዋቾች የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር መዘናጋት ተጠቅመው በብሩክ አማካኝነት የአቻነት ጎል አስቆጥረዋል።

የአቻነቱ ጎል ያነቃቸው ባህር ዳር ከተማዎች ከገቡበት መፋዘዝ ወጥተው በቶሎ ምላሽ ሰጥተዋል። ግቡ ከተቆጠረ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ግርማ ዲሳሳ ከመስመር የመታውን ኳስ የወልዋሎ የተከላካይ መስመር ተጨዋች ሳሙኤል ዩሃንስ በራሱ ላይ በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። (ዳኛው በግርማ ዲሳሳ ነው የግቡን ባለቤት የመዘገቡት)። ይህቺ ጎል በተቆጠረችበት ቅፅበት የወልዋሎ ዓ/ዩ ተጨዋቾች ጨዋታውን አንቀጥልም በማለት ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል። ግቡ ከመቆጠሩ በፊት የተጎዳ ተጨዋች ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለቆ ሳይወጣ ለምን ጨዋታው ጀመረ በሚል እንዲሁም ዳኛው ጨዋታውን በአግባቡ አልመራም በማለት ጨዋታውን ያቋረጡ ሲሆን የእለቱ ኮሚሽነር ኮ/ር ጌታቸው የማነብርሃን የቡድኑን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እና ተጨዋቾችን አረጋግተው ከ12 ደቂቃዎች ውዝግብ እና ጭቅጭቅ በኋላ ጨዋታው ጀምሯል።


ጨዋታውን ባቋረጠው ምክንያት ክስ አሲዘው ወደ ሜዳ የተመለሱት ወልዋሎዎች ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ ይበልጥ ጫናዎችን ፈጥረው ተጫውተዋል። በተለይ ተቀይሮ በገባው ሰመረ ሃፍተይ አማካኝነት ከየአቅጣጫው የአቻነት ግቦችን ሲፈልጉ ታይተዋል። በተቃራኒው የመሪነት ግብ ካገኙ በኋላ እጅግ አፈግፍገው የተንቀሳቀሱት ባህር ዳሮች የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች በጫናዎች ውስጥ አሳልፈዋል።

ተቀይሮ የገባው ሰመረ በ80 እና በ81ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ለማስቆጠር ጥሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ያላቸውን መሳሪያ ሁሉ ለመጠቀም የሞከሩት ወልዋሎዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃ እጅግ ለግብነት የቀረበ እድል አምልጧቸዋል። ጁኒያስ ናንጂቦ ከመሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ወጥቼ እይዛለሁ ያለው ሃሪሰን ሄሱ ሜዳው አንሸራቶት ወድቋል። ነገር ግን በመዘናጋት ስሜት ውስጥ ወደ ኳሱ ሲሮጥ የነበረው ጁኒያስ ናንጂቦ ኳሱ ላይ ሳይደርስበት ባዶ መረብ አምልጦታል። ጨዋታውም በባለሜዳዎቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ውጤቱን ተከትሎ በ11 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ባህር ዳሮች ነጥባቸውን 14 በማድረስ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ተጋባዦቹ ወልዋሎዎች በበኩላቸው ከነበሩበት 3ኛ ደረጃ 1 ደረጃ ተንሸራተው በ14 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ