የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 3-2 ወልዋሎ ዓ/ዩ

አምስት ግቦች ከተቆጠሩበት የባህር ዳር ከተማ እና የወልዋሎ ዓ/ዩ ጨዋታ በኋላ የባለሜዳዎቹ ቡድን አሰልጣኝ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የወልዋሎው ዮሐንስ ሳሕሌ ሳይሰጡ ቀርተዋል።


👉 “ከባለፈው ጨዋታ ስሜት መውጣት ስለነበረብን ማሸነፋችን ደስ ብሎኛል” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ረጃጅም ኳሶች እና ብዙ የአካል ንክኪ የበዛበት ጨዋታ ነበር። ማሸነፋችን ግን ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም ከባለፈው ጨዋታ (የሲዳማ ቡና) ስሜት መውጣት ስለነበረብን። በእኛ በኩል በእንቅስቃሴ ደረጃ ብቅ ጥልቅ የሚል ነገር አይቻለሁ። ለወደፊቱም ገና ብዙ የምናስተካክላቸው ነገሮች እንዳሉ ተመልክቼበታለሁ።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተከተሉት ስልት

ተጋጣሚያችን ረጃጅም ኳሶችን ስለሚጠቀም ክፍተቶችን ለመዝጋት ሞክረናል። በተለይ በመጨረሻው ተከላካያችን እና በግብ ጠባቂያችን መካከል ቦታዎችን አግኝተው እንዳይጠቀሙ ጥረናል። ነገር ግን እኛ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ባለመጠቀማችን ተጋጣሚያችን ቶሎ ቶሎ እንዲያጠቃን ሆኗል። በአብዛኛው ግን ተጨዋቾቼ ጨዋታውን እየመሩ ስለነበረ እና ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት በተፈጠረባቸው ጉጉት ወደ ኋላ አፈግፍገው ተጫውተዋል። ወደ ፊት ግን ጨዋታውን በጀመርንበት ፍጥነት እና ኃይል ማጠናቀቅ እንዳለብን ይሰማኛል።

ቡድኑ እየመራ ግብ ስለሚያስተናግድበት ምክንያት

የተከላካይ ክፍሉ መዘናጋት ሳይሆን መሸሹ ነው ዋጋ እያስከፈለን ያለው። ጎሎች ካገባን በኋላ ለተጋጣሚያችን በቂ የመጫወቻ ቦታ እየሰጠን ነው ግቦችን እያስተናገድን ያለነው። ይህንን ለመቅረፍ በልምምድ ሜዳ ላይ እየተነጋገርን ነው። ወደ ፊት ይህንን ችግራችንን ቀርፈን ከሜዳችን ውጪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ መልመድ አለብን።

ከደሞዝ ጋር በተገናኘ ቡድኑ ላይ እየተፈጠሩ ስላሉ ነገሮች?

ይህ አስተዳደራዊ ጉዳይ ነው። እንደዚህ አይነት ጥያቄ ከተጨዋቾች ሲመጣ የቡድን ግንባታ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። የክለቡ ቦርድ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንክሮ እየሰራ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን የከተማው መስተዳደር ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ሊያየው ይገባል።

*የወልዋሎ ዓ/ዩ አሰልጣኝ ሃሳባቸውን ለጋዜጠኞች ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ