ሀብታሙ ታደሰ ደሞቆ በዋለበት የ9ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን በመርታት በሜዳው ያለውን የበላይነት አስቀጥሏል።
ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት በፋሲል ከተማ 2-1 ከተሸነፈው የቡድን ስብስብ ውስጥ ጉዳት ባስተናገደው አቡበከር ናስር ምትክ እንዳለ ደባልቄን ብቻ ሲቀይሩ በተመሳሳይ ሲዳማ ቡናዎች ባህርዳር ከተማን 3-1 ከረታው የቡድን ስብስብ የመስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለን በዮናታን ፍሰሀ ብቻው ተክተው ለዛሬው ጨዋታ መቅረብ ችለዋል።
በከፍተኛ ውጥረት ታጅቦ የተካሄደው የሁለቱ ጨዋታ በርከት ባሉ የግብ ሙከራዎች ባይታጀብም ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር የታየበት ነበር። እንግዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች ገና ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ኳስን ከራሳቸው ሜዳ እንዳይጀምሩ ከፍተኛ ጫና በማሳደር የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ለስህተት ለመዳረግና ኳሶችን በአደገኛ ቀጠናዎች ላይ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ያደረጉት ጥረት በተለይ በ4 አጋጣሚዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የሰመረላቸው ቢሆንም ኳሱን በመጠቀም ረገድ በተጫዋቾች ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ኳሶቹ ሲባክኑ ተስተውሏል።
የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ነበሩ። በ5ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ከግራ መስመር አጥብቦ ከሲዳማ ሳጥን ጠርዝ አክርሮ ወደ ግብ የላካትን ኳስ መሳይ አያኖ በግሩም ብቃት ሊያድንበት ችሏል። በሲዳማ ቡናዎች በኩል በ20ኛው ደቂቃ የተከላካይ አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት አክርሮ የመታውና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
በ23ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን ከቀኝ መስመር ወደ መሐል ያሳለፈለትን ኳስ እንዳለ ደባልቄና ሀብታሙ ታደሰ ጨራርፈው ወደ ግብ ልከዋት የሲዳማው ቡና ግብጠባቂ መሳይ አያኖ እንደምንም ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
በቡናዎች በኩል ከሰሞኑ ወደ ቋሚ 11 ውስጥ መካተት የቻለው ሀብታሙ ታደሰ ከቀኝ መስመር እየተነሳ በጥልቀት ወደ ኃላ ተስቦ ኳሶች የሚያራጅበት መንገድ እንዲሁም በመስመሮች በኩል አደጋ ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት እጅግ አስደናቂ ነበር።
ሲዳማ ቡናዎችም በሀብታሙ ገዛኸኝ በሚገኝበት የቀኝ መስመር በኩል ባጋደለ ሁኔታ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተመሳሳይ አዲስ ግደይና ይገዙ ቦጋለ ቦታ እየተቀያየሩ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮችን ጫና ውስጥ ለመክተት የሚያደርጉት ጥረት በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ መልካም የሚባል ነበር።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሲል ሐብታሙ ታደሰ ከቀኝ መስመር ወደ ሲዳማ ሳጥን ከገባ በኃላ በግርማ በቀለ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እንዳለ ደባልቄ አስቆጥሮ ቡድኑ መሪ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አስችሏል።
ፍፁም ቅጣት ምቱ በተሰጠበት ወቅት የሲዳማ ቡናው የመስመር ተከላካይ ተስፉ ኤልያስና ዮሴፍ ዮሐንስ ውሳኔውን በመቃወም ያሳዩት ተግባር በስታዲየሙ የታደመውን የእግርኳስ አፍቃሪ ያስቆጣ ነበር። ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት የመሩት ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃም ሁኔታውን ለመቆጣጠር በእጅጉ ከብዷቸው የተስተዋለ ሲሆን ህግ ከተመገርጎም ባለፈ ራሳቸውን ለማስከበር ተቸግረው ተስተውለዋል።
በጨዋታው የዕረፍት ሰዓት 22ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን እያከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበርን ለመዘከር የተዘጋጀውን ኬክ የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የቆረሱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ማኅበሩን በተለያዩ ኃላፊነቶች እያገለገሉ ለሚገኙት አመራሮችና ለክለቡ ፕሬዚዳንት የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ 51ኛው ደቂቃ በግሩም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘችውን ኳስ አዲስ ግደይ በቄንጥ አሳልፎለት ዳዊት ተፈራ ፍፁም እርጋታ በተሞላበት ድንቅ አጨራረስ ሲዳማ ቡናን አቻ ማድረግ ችሏል።
በግቧ መቆጠር የተነቃቁ የሚመስሉት ሲዳማ ቡናዎች በሰንደይ ሙቱኩና አበባየሁ ዮሐንስ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ኢትዮጵያ ቡና ለግቧ አፀፋ ለመስጠት 7 ያክል ደቂቃ ነበር የፈጀባቸው። ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ሳይጠበቅ ከሲዳማ ተከላካዮች በላይ አስደናቂ ዝላይ በማድረግ በግንባሩ ማራኪ ኳስ በማስቆጠር ቡድኑን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛዋ ግብ መቆጠሯ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታው ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ ቡናዎች እንዲያጋድል ምክንያት የሆነ እስኪመስል ድረስ በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡና ፍፁም የበላይ ነበሩ። ሆኖም በተደጋጋሚ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ኢትዮጵና ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በተለይም በ65ኛው ደቂቃ በጨዋታው የደመቀው ሀብታሙ ታደሰ ከተከላካይ ያሳለፈለትን ኳስ ሚኪያስ መኮንን የሞከረውና መሳይ ያዳነበት እንዲሁም በ76ኛው አህመድ ረሺድ ከቀኝ ያሳለፈለትን ኳስ ሀብታሙ ሞክሮ በተመሳሳይ ያመከነበት ኳስ በተጨማሪ በ80ኛው ደቂቃ ሀብታሙ በቄንጥ ያቀበለውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ ከመሳይ ጋር ተገናኝቶ መሳይ ቀድሞ ደርሶ ያመከነበት ኳስ ተጠቃሽ ሆኑ እንጂ እንደወትሮው ሁሉ በሁለተኛ አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በርካታ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር።
ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና 3ኛ ተከታታይ ጨዋታውን በሜዳው ማሸነፍ ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ