ሪፖርት| ቻምፒዮኖቹ መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ድል አስመዘገቡ

በሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት በሜዳቸው ሰበታ ከተማን ያስተናገዱት መቐለ 70 እንደርታዎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ከተከታዮቻቸው ያላቸውን ልዩነት አስፍተዋል።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ወልቂጤን ካሸነፈው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ሲጀምሩ ሰበታዎች ጅማን ካሸነፈው ስብስብ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሳሙኤል ታዬን በጌቱ ኃይለማርያም እና ሲይላ ዓሊ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመርያው አጋማሽ መቐለዎች ውጤታማው ቀጥተኛ አጨዋወታቸውን ይዘው ሲገቡ ሰበታዎች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

በመጀመርያው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል አታሎ ገብቶ በመምታት ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ከደቂቃዎች በኃላም ዮናስ ገረመው በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን ገብቶ መቶ ዳንኤል አጄይ ባዳነበት ሙከራ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በአስራ ሶስተኛው ደቂቃም ኦኪኪ ኦፎላቢ ዮናስ ገረመው ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በክረምቱ ክለቡን የተቀላቀለው ናይጄርያዊው አጥቂ ይህ ጎል በዘንድሮው ሊግ የመጀመርያ ሆኖ ተመዝግቦለታል።

መቐለዎች ከግቡ በኃላም በተመሳሳይ በኦኪኪ ኦፎላቢ የግንባር ኳስ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ዳንኤል አጄይ መልሶባቸዋል።

በአጋማሹ አብዛኛውን ግዜ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት ሰበታዎች የመቐለን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ሙከራ ለማድረግ እና ንፁህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። በዚህም ሲላ ዓሊ ከቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ ውጭ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ከመጀመርያ አጋማሽ የተሻለ ጥሩ ፉክክር መንፈስ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሰበታዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱበት ቢሆንም ሙከራዎች በማድረግ ግን መቐለዎች የተሻሉ ነበሩ። በ46ኛው ደቂቃም ኦኪኪ ኦፎላቢ ከሥዩም ተስፋዬ የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በማስቆጠር በማስቆጠር የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በመልሶ ማጥቃት እና ቀጥተኛ አጨዋወት የግብ ዕድል ለመፍጠር ያልተቸገሩት መቐለዎች ከግቡ በኃላም በትጠቀሱት አጨዋወቶች ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ያሬድ ከበደ በመስመር ይዞ ገብቶ በመምታት ወንድፍራው ጌታሁን ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ እና ያሬድ ከበደ ያሬድ ብርሀኑ ያሻገረለት ኳስ በትኩረት ማጣት ያልተጠቀመበት ንፁህ የግብ ዕድል ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው አጋማሽ በብዙ ረገድ ተሻሽለው የተመለሱት ሰበታ ከተማዎችም በተለይም የተጫዋቾች ቅያሪ ካደረጉ በኃላ በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ፍርዳወቅ ሲሳይ በሁለት አጋጣሚዎች ከመስመር አሻምቶ አንተነህ ገብረክርስቶስ እና አሌክስ ተሰማ እንደምንም ያወጧቸው ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ። በሰማንያ አራተኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው እንዳለ ዘውገ በጥሩ ምት ግሩም ግብ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና የፈጠሩት ሰበታዎች ከግቡ በኃላ ከጥረት የዘለለ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩበት ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም ኦኪኪ ኦፎላቢ አታሎ ወደ ሳጥን በመግባት መቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት ኳስ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በዳንኤል አጃይ ድንቅ ብቃት ከፍፁም ቅጣት ምት ወደ ጎልነት ያልቀየረው ዕድል ይጠቀሳሉ።

ውጤቱን ተከትሎ መቐለዎች ነጥባቸውን ከፍ አድርገው መሪነታቸውን ሲያጠናክሩ ሰበታዎች በነበሩበት ነጥብ ረግተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ