ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኋላ ጣፋጭ ድል አሳካ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ሀዋሳ በሜዳው ወልቂጤ ከተማን አስተናግዶ 3ለ1 በመርታት ከአምስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ወሳኝ ሙሉ ነጥብን አሳክቷል፡፡

ሀይቆቹ ወደ አዳማ ተጉዘው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ውስጥ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ብርሀኑ በቀለን ወደ ተጠባባቂ በማውረድ አለልኝ አዘን እና ሄኖክ አየለን አስገብተዋል፡፡ በመቐለ በሜዳቸው በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ተሸንፈው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ወልቂጤዎች በበኩላቸው ሦስት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ ይድነቃቸው ኪዳኔ፣ አሳሪ አልመሀዲ እና ሄኖክ አወቀን አስወጥተው ሶሆሆ ሜንሳህ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ዓባይነህ ፊኖን ተክተዋል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በሀዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ ላደገው እና ዐምና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ወደ ልጅነት ክለቡ ሀዋሳ ተመልሶ ለተጫወተው የአሁኑ የወልቂጤ ተጫዋች እና ረዳት አሰልጣኝ አዳነ ግርማ ከሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ስጦታ ተበርክቶለታል፡፡

ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ቀዳዳን ፈልጎ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ከመድረስ ይልቅ መሀል ላይ የተገደቡ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን አልፎ አልፎ በረጅሙ ከሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ግን ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ፡፡ 11ኛው ደቂቃ ላይ ምንም እንኳን ኢላሚዋን የጠበቀች ባትሆንም ተስፋዬ መላኩ የሰጠውን ኳስ ብሩክ በየነ በአየር ወደ ግብ ልኳት የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት ተጠቃሽ አጋጣሚ ናት፡፡

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ የተሻለ የሜዳ ላይ የማጥቃት አማራጭን እንመለከታለን ብንልም ታይቶ ከሚጠፋ እንዲሁም ደግሞ የሚቆራረጡ ኳሶችን ከማየት ውጪ ጥርት ያሉ ነገሮች ለማስተዋል ግን አልቻልም። ይሁን እንጂ በወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች መዘናጋት የመጀመሪያዋን ግብ 20ኛው ደቂቃ ላይ አይተናል፡፡ ከማዕዘን ምት ዳንኤል ደርቤ ሲያሻማ አለልኝ አዘነ በእግሩ አመቻችቶ ሰጥቶት ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ በግንባር በመግጨት የቀድሞው ቡድኑ ላይ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ ብሩክ ግቧን ካስቆጠረ በኃላ ለቀድሞው ቡድኑ ያለውን ክብር ደስታውን ባለመግለፅ አሳይቷል፡፡

ግብ ለማስተናገድ የተገደዱት ወልቂጤዎች ከግቧ በኃላ በረጃጅም ኳስ ወደ ጃኮ አራፋት አዘንብለው መጫወትን ምርጫቸው ቢያደርጉም አጥቂው ጠጣሩን የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል በተለይ የመሀል ተከላካዩ ላውረንስ ላርቴን አልፎ ማስቆጠር ላይ ተስኖት ታይቷል፡፡ ይሁን እና ብልጠቱን ተጠቅሞ በመልሶ ማጥቃት ጃኮ አራፋት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽራለች፡፡ ተጨማሪ ግብ ለማከል በቀኝ መስመር በኩል በዳንኤል ደርቤ ተሻጋሪ ኳስን ለመጠቀም ሀዋሳዎች ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይ በዚሁ መስመር ዳንኤል በረጅሙ አሻግሮ ሄኖክ አየለ በግንባር ገጭቶ የላይኛው የግቡ ብረት የመለሰችበት ምናልባትም የሀዋሳን የግብ መጠን ከፍ ልታደርግ የምትችል አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ ደበዘዝ ያለ እንቅስቃሴ በሚገባ ተሻሽሎ የቀረበ የተነቃቃ የሚመስል ቡድንን በሁለቱም በኩል ያየንበት ነበር፡፡ ለዚህም ማሳያ ወልቂጤዎች ገና ሁለተኛው አጋማሽ የዳኛው ፊሽካ እንደተሰማ ያስቆጠሯት ግብ ምስክር ነች። በቅብብል ወደ ሀዋሳ ሳጥን በፍጥነት መድረስ የቻሉት ዕንግዳዎቹ የተከላካዮቹን መዘንጋት ተከትሎ ጃኮ አራፋት አመቻችቶ የሰጠውን ሁለት ጊዜ ብቻ ገፋ አድርጎ ጫላ ተሺታ ከመረብ አሳርፎ ወልቂጤን አቻ አድርጓል፡፡

ወልቂጤ ከተማዎች ምንም እንኳን ግብ ያስቆጥሩ እንጂ የዳንኤል ደርቤን መጎዳት ተከትሎ ተቀይሮ የገባው አማካዩ ዘላለም ኢሳይያስ ከአማካዮቹ አለልኝ አዘነ እና ሄኖክ ድልቢ ጋር በሚገባ ተዋህዶ የፈጠረው ቅንጅት ሀዋሳዎች በጨዋታው ብልጫ እንዲወስዱ ረድቷቸዋል፡፡ 64ኛው ደቂቃም ልዩነት ፈጣሪው ዘላለም ከሄኖክ ጋር አንድ ሁለት ከተቀባበሉ በኋላ ብሩክ ጋር የደረሰውን ኳስ ብሩክ የግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ስህተት ታክሎበት ለራሱም ለክለቡም ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

በይበልጥ የጨዋታውን እንቅስቃሴ እየተቆጣጠሩ የመጡት ሀዋሳ በብሩክ በየነ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ተባረክ ኢፋሞ ሙከራን ያደረጉ ሲሆን ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ አድኖባቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት እና በሀዋሳ ለመበለጥ የተገደዱት ወልቂጤዎች በአንፃራቸው ጫላ ተሺታ እንዲሁም ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን ካደረጉት ሁለት ቀላል ሙከራዎች ውጪ ይህ ነው ሚባል የጠራ ዕድልን ሲያገኙ አላየንም፡፡

በአንፃሩ ተጨማሪ ግብን ለማስቆጠር ሲታትሩ የነበሩት ሀይቆቹ ሦስተኛ ግባቸውን 86ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል፡፡ ከቀኝ በኩል ሁለት ግብን ያስቆጠረው ብሩክ በየነ ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ሄኖክ አየለ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፏታል፡፡ ሄኖክ አየለም በሀዋሳ መለያ የመጀመሪያ ግቡን ከመረብ አዋህዷል፡፡

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠር ጨወታው በሀዋሳ 3ለ1 አሸናፊነት መደምደሙን ተከትሎ ሀዋሳ ደረጃውን ከፍ ሲያደርግ ወልቂጤ የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ