ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

ድሬዳዋ ከተማ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ታግዞ አዳማ ከተማን 2-1 መርታት ችሏል።

በብርቱካናማዎቹ በኩል ባለፈው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ በፍሬው ጌታሁን፣ ዘሪሁን አንሼቦ እና ባጅዋ አዴገሰን ምትክ ሳምሶን አሰፋ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ሙህዲን ሙሳ ወደ አሰላለፉ ሲካተቱ በአዳማ በኩል በሜዳው ከሀዋሳ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ሱሌይማን ሰሚድ እና አማኑኤል ጎበና ወጥተው ሱሌይማን መሐመድ እና ቡልቻ ሹራ ተካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በኩል በተመጣጠነ የኳስ ቁጥጥር የጀመረው ጨዋታ ብዙም ሳይቆይ ግቦች የተስተናገዱበት ሆኗል። ከዚያ ቀደም ብሎ በ6ኛው ደቂቃ የድሬዳዋ ከተማ የአማካይ መስመር ተጫዋች ያሬድ ታደሰ በግራ መስመር በኩል ወደ አዳማ የግብ ክልል በመግባት ያሻማውን ኳስ ኦዶንጎ ሬችሞንድ በጭንቅላት የሞከረው ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራው ሆኖ ተመዝግቧል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ በአዳማ የግብ ክልል በቀኝ ክንፍ በኩል የድሬዳዋው ያሲን ከማል ያሻማውን ኳስ የአዳማ ከተማው መናፍ ዐወል ለማውጣት ሲሞክር በራሱ ግብ ላይ በማቆጠሩ ምክንያት የድሬዳዋ ከተማ በጊዜ መሪ መሆን ችሏል።

የድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላም በተደጋጋሚ ጎል ለማግኘት የአዳማን የግል ክልል ለመፈተሽ ሲሞክር ቆይቶ 10ኛው ደቂቃ ላይ ኦዶንጎ ሬችሞንድ እና ሙህዲን ሙሳ በጋራ ከአዳማ ከተማ ተከላካዮች ጋር ታግለው በመግባት የፈጠሩትን አጋጣሚ ሙህዲን ሙሳ ወደ ግብ ቀይሮት የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

አዳማ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ በኩል ከድሬዳዋ ከተማ ተሽለው የታዩ ሲሆን በተለይም በቀኝ ክንፍ በኩል ቡልቻ ሹራ በተደጋጋሚ ወደ ድሬዳዋ የጎል ክልል በመቅረብ የተሻሉ ኳሶችን ለአጥቂው ዳዋ ሁቴሳ በማሻማት ረገድ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል።

31ኛው ደቂቃ ላይ ለድሬዳዋ ከተማ ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረው ሙህዲን ሙሳ 3ኛ ጎል ቢያስቆጥርም የአዳማ ከተማ ተከላካይ የሆነው መናፍ ዐወል ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የዕለቱ አልቢትር ሽረውታል። በአዳማ ከተማ በኩል የመጀመሪያ ጎል ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተለይም የአጥቂው ዳዋ ሁቴሳ ተደጋጋሚ ጥረቶች በድሬዳዋ ተከላካዮች ጎል ከመሆን ከሽፈዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ አቅራቢያ ከመሀል ሜዳ ወደ ድሬዳዋ ጎል ተሻምቶ የአዳማው ግዙፉ አማካይ ከነዓን ማርክነህ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስም አዳማዎች ልዩነቱን ለማጥበብ የቀረቡበት ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ከዕረፍት በፊት የመጨረሻው ደቂቃ ሙከራው ያልተሳካው ከነዓን ማርክነህ በቅብብሎች የተገኘውን ኳስ ተጠቅሞ 49ኛው ደቂቃ ላይ ለአዳማ ከተማ የመጀመሪያ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

አዳማ ከተማዎች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ እንዲሁም ወደ ጎል በመቅረብና ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በዳዋ ሆቴሳና በከነዓን ማርክነህ አማካይነትም ለጎል የቀረቡ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። ድሬዳዋ ከተማዎችም በኦዶንጎ ሬችሞንድ በኩል ወደ አዳማዎች የግብ ክልል በመግባት ተከላካዮችን በተደጋጋሚ ማስጨነቅ ችለዋል። የድሬዳዋ ከተማው ያሲን ጀማል በቀኝ በኩል ወደ ጎል በመግባት ለኤሊያስ ማሞ አቀብሎት ኤሊያስ ሞክሮ በአዳማ ተከላካዮች የተመለሰበት እና በድጋሚ አግኝቶት ሞክሮ በሚያስቆጭ ሁኔታ የወጣበት ደግሞ የድሬዎችን መሪነት ለማስፋት የቀረበ አጋጣሚ ነበር።

በአዳማ በኩል በመልሶ ማጥቃት ቡልቻ ሹራ ወደ ግብ ሞክሮት ለጥቂት ጎል ሳይሆን የቀረው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለተመልካች ሳቢ የሆኑ የጎል ሙከራዎችን መመልከት ብንችልም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በድሬዳዋ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱ ድሬዳዋ ከተማን ወደ 12ኛ ከፍ ሲያደርግ ሳምንቱን ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ የገባው አዳማ ከተማ ወደ 14ኛ ወርዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ