የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1–1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

👉 “አሸንፈን እንወጣለን እንጂ በአቻ ውጤት ጨዋታው ይጠናቀቃል ብለን አልጠበቅንም” ኢዘዲን ዓብደላ (የሀዲያ ሆሳዕና ምክትል አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው

እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነበር። ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ሙሉ አቅማችንን አሟጠን ሜዳ ላይ ለመጠቀም ሞክረናል፤ የታክቲክ ለውጥም በማድረግ ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም። እነርሱ ባገኙት አጋጣሚ ጎል አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። ይህ እግርኳስ ነው መቀበል አለብን። ግን ጥሩ ፉክክር ያደረግንበት እንደመሆኑ አሸንፈን ሦስት ነጥብ ይዘን እንወጣለን እንጂ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ብለን አልጠበቅንም። ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመውጣትም ሞክረን ነበር፤ አልሆነም።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ መዳከም

ልጆቹ መጀመርያ አጋማሽ ላይ ያላቸውን አቅም አሟጠው ጨርሰዋል። መጀመርያ የነበረንን ነገር አለማስቀጠላችን ትንሽ ክፍተት ፈጥሮብናል።

👉 ” የምትፈልገውን ማድረግ በማትችልበት በዚህ ሜዳ መጫወት በጣም ይከብዳል” አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

በጣም ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር። ምክንያቱም ሆሳዕና በዚህ ዓመት ነው ወደ ሊጉ የመጣው የመጫወት ፍላጎታቸው ያላቸው፣ ከተከታታይ ድል በኃላ እኛን መግጠማቸውና ሁለት አቅም ያላቸው አጥቂዎች የያዘ ቡድን በመሆኑ ሊከብደን እንደሚችል ጠብቀን ነበር። አንድ አጋጣሚ አገኙ፤ እሱንም በሚገባ በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመውታል። የምትፈልገውን ማድረግ በማትችልበት በዚህ ሜዳ መጫወት በጣም ይከብዳል። ምንም ማድረግ አልቻልንም። ከዚህም ሜዳ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች ሜዳዎችም ብመለከትም ይህ ትንሽ ይከብዳል። በአጠቃላይ ከእረፍት መልስ ያደረግናቸው ለውጦች ተሳክተውልን አንድ ነጥብ ይዘን ወተናል።

የአስቻለው ታመነ ያልተለመደ ቦታ መጫወት

አንድ ነገር ልንገርህ፤ አዎ በቡድኔ ውስጥም በብሔራዊ ቡድንም በተከላካይነት ተጫውቷል። አስቻለው በጣም አቅም ያለው፣ በግንባር የሚገጭ፣ ጉልበት ያለው ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ሁለገብ ተጫዋች ነው። ዛሬም አማካይ ሆኖ በመጫወት ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ