የአሰልጣኞች አስተያየት| መቐለ 70 እንደርታ 2 – 1 ሰበታ ከተማ

በሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት መቐለ 70 እንደርታ በኦኪኪ ሁለት ጎሎች ሰበታ ከተማን ካሸነፈ በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን ሃሳብ ሰጥተዋል።

👉 “ማሸነፍ የቡድን መንፈሳችንን ያሳድግልናል”
ገ\መድህን ኃይሌ (መቐለ 70 እንደርታ)

ስለ ጨዋታው

የዛሬ የጨዋታ እቅዳችም መሪነታችን ለማጠናክር ነበር። ጨዋታውን አሸንፎ የቡድኑ የማሸነፍ መንፈስ ማጠናከር አልመን ነበር የገባነው። ከተከታዮቻችን በነጥብ በልጠን መሄድ አለብን፤ ካሁኑ ነጥብ ካልሰበሰብን ሊያስቸግረን ይችላል። የግድ በሜዳችን የምናደርገው ጨዋታ ማሸነፍ አለብን ብለን ስላሰብን ትንሽ ጉጉት ነበር። ብዙ ችግሮችም ነበሩብን።

በኳስ ቁጥጥር እነሱ የተሻሉ ነበሩ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ግን እኛ የተሻልን ነበርን። ከዚህ በላይም ግብ ማስቆጠር እንችል ነበር። የተጋጣሚን ስህተት ተጠቅሞ ዕድሎች በመፍጠር ብዙ ነገር ይቀረን ነበር። ባጠቃላይ ሲታይ ግን ጥሩ ነው፤ መጥፎ አደለም። ማሸነፍ የቡድን መንፈሳችን ያሳድግልናል።

በአጠቃላይ ሲታይ ሰበታዎች ብልጫ ወስደውብናል። ይህ ሜዳ ለሁሉም አንድ ነው። የመጫወቻ ሜዳው ጥሩ ሰለሆነ ለሁሉም ይመቻል፤ እነሱም ተመችቷቸው ጥሩ ጨዋታ ተጫውተዋል። አሸንፈን ስለወጣን ደስ ብሎኛል።

ስለ ኦኪኪ

ኦኪኪ ከግብ ርቆ ስለነበር እንደ አጥቂ ትንሽ መረበሾች ነበሩበት። ዛሬ ግን ከሁለት በላምይ ማግባት ይችል ነበር። ወደ ግብ ማግባት መመለሱም በቀጣይ የማጥቃት ኃይልችን በተሻለ ያጠናክርልናል።

👉 “ከማሸነፍ መሸነፍ በላይ እንቅስቃሴውን ነው ማየት ያለብን” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ከሜዳ ውጭ ጨዋታ እንደመሆኑ እንቅስቃሴያችን መጥፎ አይደለም። አሁንም የምናርማቸው ስህተቶች አሉ፤ በተለይም ከመከላከል ጋር ተያይዞ። ጎሎች የሚቆጠሩትም አደጋዎች የሚፈጠሩትም በቀላሉ ነው። እነሱን ማሻሻል ይገባናል። በተለይም ከነዚ አይነት ጠንካራ አጥቂዎች ካሉት ቡድን ጋር ስትጫወት ስህተቶች የምትሰራ ከሆነ ትቀጣለህ። በእንቅስቃሴ ደርጃ ግን መጥፎ አይደለም።

ቡድኑ ስላለበት ደረጃ

አሁን ስለደረጃ ማውራት ከባድ ነው። በርካታ ጨዋታዎች ከፊታችን አሉ። እከሌ ወራጅ ነው እከሌ እንዲ ነው ማለት አይቻልም። ከማሸነፍ መሸነፍ በላይ እንቅስቃሴው ነው በበለጠ ማየት ያለብን። እንቅስቃሴያችን ከግዜ ግዜ የሚሻሻል ስለሆነ ብዙም ስጋት የለንም።

ስለ ተጋጣሚ አጨዋወት

ቀጥተኛ አጨዋወታቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል።
በተለይም ሦስቱ አጥቂዎች ፈጣኖች ናቸው። ከጎል ጋር ያላቸው ነገርም ጥሩ ነው። ከመስመር በሚነሱ ኳሶችም ጥሩ ናቸው። ጎሎቹም በዛ መንገድ ነው የገቡት ይሄንን መመስከር ይቻላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ