የአሰልጣኝ አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 2-1 አዳማ ከተማ

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማን ያገናኛው የዛሬው የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የድሬዳዋው አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል። በአዳማ ከተማ በኩል ግን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማካተት አልተቻለም።

👉 “ጨዋታው ሁለት መልክ ቢኖረውም ከዕረፍት በፊት ጥሩ እንቅስቃሴ አርገናል ብዬ አስባለው” ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታውን እንዳያችሁት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው ነገር ፈፅሞ የተለያየ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለን ነበር፤ በፍጥነትም ነበር ጎል ያስቆጠርነው። በእንቅስቃሴም ደረጃ ጥሩ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ቡድኔ ጥሩ አልነበረም ፤ የሚታይ ነገር ነው። ግን ያው የምገነዘበው ነገር አለ። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት መጥተን ነው ይህን ጨዋታ ያደረግነው። ሁለተኛ አዳማ ከነበረበት ችግር አንፃር መቶ ፐርሰንት እናሸንፋለን የሚል ግምት የነበረ ይመስለኛል። ያ ተጫዋቾቹ ላይ ጫና ነበረው። ያው ጨዋታው ሁለት መልክ ቢኖረውም ከዕረፍት በፊት ጥሩ እንቅስቃሴ አርገናል ብዬ አስባለው።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች እና ስለቡድኑ ግብ የማስተናገድ ችግር

አሁን እየተመለከትኩት እናዳለሁት ከሜዳ ውጪ ስንጫወት ጥሩ ነን። ድሬዳዋ ከምናደርገው የተሻለ እንቅስቃሴ እናደርጋለን ፤ የጊዮርጊሱን ጨዋታ መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን ያ ዋጋ የለውም። ዋጋ የሚያስከፍሉንን ችግሮች ማስተካከል ይኖርብናል። ሁል ጊዜ እያገባን ግባችንን መጠበቅ ካልቻልን ዋጋ የለውም። አንድ አግብተን ሁለት ፣ ሁለት አግብተን ሦስት ሊገባ ይችላል። ስለዚህ ይህን ነገር ለማስተካከል መስራት ይኖርብናል። ባሉት ተጫዋቾች መስራት የምንችለውን ያህል እንሰራለን።

በቀጣይ መሻሻል ስለመቻሉ...

አራት ቀን ልምምድ ሳይሰሩ ይህን ያህል መንቀሳቀሳቸው (አዳማዎች) ውድድሩ ከባድ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። እኛም በተፅዕኖ ውስጥ ገብተን ቢሆን ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ልናደርግ እንችል ነበር። በስሑል ሽረም ማየት እንችላለን ፤ ታች ነበር ዛሬ ግን ሦስተኛ ነው። ስለዚህም ከባድ አይደለም። አንድ ጊዜ ወደ ላይ የሚወጣበት በመሆኑ ከባድ አይደለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ