ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ከአስከፊ የውጤት ጉዞ በኋላ ጣፋጭ የሜዳ ውጪ ድል ተቀዳጅቷል

በጅማ ዩኒቨርስቲ የተደረገው የጅማ አባጅፋር እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በተጋባዦቹ ድቻዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጊዜያዊው አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድልን ለድቻ አስገኝቷል።

በባለሜዳዎቹ በኩል ባለፈው ሳምንት በሰበታ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ በወንድማገኝ ማርቆስ እና ሀብታሙ ንጉሴ ምትክ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ብዙዓየሁ እንደሻው በመጀመርያ አሰላለፍ ሲካተቱ በእንግዶቹ በኩል በአዛርያስ አቤል፣ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ተመስገን ታምራት ምትክ ያሬድ ዳዊት፣ ውብሸት ዓለማየሁ እና እንድሪስ ሰዒድ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ተጋባዦቹ ወላይታ ድቻዎች በኳስ ቁጥጥር እና ወደ ጎል በመድረስ ከባለሜዳዎቹ ተሽለው ታይተዋል። በተለይ ቡድኑ በባዬ ገዛኸኝ እና ቸርነት ጉግሳ ሙከራዎች ጎሎችን ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተሏል። ጨዋታው በተጀመረ በ19ኛው ደቂቃም እድሪስ ሰዒድ በቀኝ መስመር ለባዬ ባሻገረው ኳስ የጦና ንቦቹ ወደ ግብ ቀርበው ነበር።

በተቃራኒው ወደራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት ጅማዎች ረጃጅም ኳሶችን ለብዙዓየሁ እና መሐመድ ያኩቡ በመላክ ግቦችን በራሳቸው መንገድ ለማግኘት ጥረዋል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም ከረጅም ኳስ ያገኘውን አጋጣሚ በመግፋት ወደ ሳጥን ያመራው ብዙዓየሁ ወደ ግብ ሊመታ ሲል በተከላካዮች ተነክቶ ሲመለስ ያገኘው ሱራፌል አወል ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መትቶ ጥሩ ጎል አስቆጥሯል።

ጨዋታው በሚፈልግላቸው መንገድ እየተጓዘላቸው የመጣው ጅማዎች ኳስን ለተጋጣሚያቸው በመተው መከላከላቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግልፅ የግብ ማግባት እድል ሳይፈጠርበት በባለሜዳዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ የነበሩት ድቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ቶሎ ለመመለስ ጥረቶችን ማድረግ ቀጥለዋል። በተለይ ኳስን በአላማ በመቀባበል ጥብቁን የጅማን የመከላከል አደረጃጀት ለመሰባበር ጥቃቶችን መሰንዘር ጀምረዋል።

በይበልጥ በባዬ እና እድሪስ አማካኝነት ወደ ጅማ የግብ ክልል ሲደርሱ የታዩት ድቻዎች በ67ኛው ደቂቃ በተፈጠረ የተከላካይ እና የግብ ጠባቂ መዘናጋት ስህተት ባዬ ገዛኸኝ ግብ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል። ይህ ግብ ያነቃቸው ጅማዎች በተለይ በመስመሮች በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ድቻ ግብ ለመድረስ ጥረዋል። በተቃራኒው የአቻነት ግብ ያስቆጠሩት ድቻዎች ከነበራቸው የኳስ የበላይነት ተቆጥበው በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል።

ጨዋታው ሊጠናቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ያሬድ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት እድሪስ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች በቀሩት ጊዜም ፀጋዬ ብርሃኑ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ተከላካዮች ከመስመር አወጣበት እንጂ የወላይታ ድቻ መሪነት ለመስፋት ተቃርቦ ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በተጋባዦቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ 10 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ጅማ ወደ 11ኛ ደረጃ ሲንሸራተት የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የነበረው ወላይታ ድቻ ነጥቡን 9 በማድረስ 13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ