የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ወላይታ ድቻ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የድቻው ጊዜያዊ አሰልጣኝ አስተያየት ሲሰጡ የጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

👉 ” ተጫዋቾቹ ላይ ጥሩ መነሳሳት መፍጠር ችለናል” ደለለኝ ደቻሳ (ወላይታ ድቻ)

ስለጨዋታው

ጨዋታውን እንዳያችሁት ነው። ጅማ በሜዳው ከባድ ነው ፤ እኛም በተከታታይ ከሽንፈት ነው የመጣናው ነገር ግን ከሶዶ ስንነሳ ጀምሮ በሥነ-ልቡናው ልጆቻችን ላይ ስንሰራ ነበር። ወጣቶች ናቸው፤ ፍራቻም ነበር። ነገር ግን ደጋፊው ከዛም መጥቶ ድጋፍ ስላደረገልን ጥሩ ነገር አሳይተናል። ለጅማ አካባቢ ስፖርት አፍቃሪም ጥሩ ነገር አሳይተናል ብዬ አስባለው። በቀጣይ በድክመቶቻችን ላይ ሰርተን የተሻለ ነገር ይዘን እንቀርባለን ብለን እናስባለን።

ክለቡ ውስጥ ስላለው አስተዳደራዊ ችግር

የአስተዳደራዊ ጉዳይ በአስተዳደሩ የሚስተካከል ነው። እኛ እንደአሰልጣኝ ቡድን አባላት ተጫዋቾቻችን ላይ እየሰራን ነው። እንዳያችሁትም ተጫዋቾቹ ላይ ጥሩ መነሳሳት መፍጠር ችለናል። ይህን መነሳሳት ይዘንም በቀጣይ ጥሩ ነገር እንደምንሰራ ነው የምናስበው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ