ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፩) | ክለብ ትኩረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዓርብ እና ቅዳሜ በተደረጉ ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል መቐለ መሪነቱን ያጠናከረበትን፤ ስሑል ሽረ በአስደናቂ ጉዞው የቀጠለበትን፤ ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ከተከታታይ ውጤት ማጣት በኋላ የተመለሱበትን ድሎች አስመዝግበዋል። እኛም በዚሁ ሳምንት ከነበሩ ሁነቶች መካከል በክለብ ትኩረት አምዳችን ዋና ዋና ነጥቦችን በተከታዩ መንገድ አሰናድተናል።

👉 የስሑል ሽረ አስደናቂ መነቃቃት

በሊጉ ጅማሮ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ መልካም አጀማመር ቢያደርግም ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግር መጠነኛ መንገራገጮች ገጥመውት ነበር። ነገር ግን ቀስ በቀስ ለውጦችን በማሳየት በዚህኛው ሳምንት ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል፤ ድሉን ደግሞ ጣፋጭ የሚያደርገው በሊጉን ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ በሆኑት ፋሲል ከነማዎች ላይ የተገኘ መሆኑ ነው።

አለመሸነፍን ተቀዳሚ አማራጭ በማድረግ በኡሉታዊ አቀራረባቸው የተነሳ ትችቶች ሲያስተናግዱ ቢቆዩም በተከታታይ ባደረጓቸው ጨዋታዎች በድንቅ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሰበታ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማን በማሸነፍ ከወረጅ ቀጠና ስጋት በመላቀቅ ወደ ሰንጠረዡ አናት መጠጋት ችለዋል። በተለይም በዓርቡ የፋሲል ከተማ ጨዋታ ላይ ቡድኑ በጨዋታው በርካታ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር።

👉 የወላይታ ድቻ መነሳሳት

ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር በሳምንቱ አጋማሽ በስምምነት የተለያዩት ወላይታ ድቻዎች በ9ኛ ሳምንት ወደ ጅማ ተጉዘው በጊዜያዊው አሰልጣኝ ደሳለኝ ደቻሳ እየተመሩ ከመመራት ተነስተው ጅማ አባጅፋርን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።

እንደተጠበቀውና አብዛኛዎቹ አሰልጣኝ አሰናብተው በሌላ የሚተኩ ቡድኖች ሲያደርጉ እንደሚስተዋለው ወላይታ ድቻዎች ከገ/ክርስቶስ ስንብት ማግስት በፍጥነት ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ እንደሚገኙ አሳይተዋል። ከመመራት ተነስተው ማሸነፋቸው እና ድሉ ከሜዳቸው ውጪ መሆኑም ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው።

የጦና ንቦቹ በሜዳው ለመግጠም እጅግ አስቸጋሪ የሆነው ጠንቃቃውን የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ቡድን በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከመመራት ተነስቶ ማሸነፍ የማንሰራራት ጉዟቸውን “ሀ” ብለው የጀመሩ ይመስላል።

👉 የወልዋሎ ተጫዋቾች ተቃውሞ

ቡድናቸው በባህር ዳር ከተማ 3-2 በተሸነፈበት ጨዋታ የወልዋሎ ተጫዋቾች በ68ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዮሐንስ በራሱ ላይ ያስቆጠራትና (የተመዘገበው በግርማ ዲሳሳ ነው) ለባህር ዳር ከተማ 3 ነጥብ ካስገኘችው ግብ መቆጠር በኋላ ጨዋታውን በመሩት ዳኞች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል።

ሜዳ ለቆ እስከመውጣት በደረሰው ተቃውሟቸው ግቧ በተቆጠረችበት የጨዋታ ሂደት የተጎዳ ተጫዋች ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለቆ ሳይወጣ ጨዋታው እንዲቀጥል መደረጉ እንዲሁም ጨዋታውን በአግባቡ እየመሩ አይደለም በሚል ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ለ12 ደቂቃ ያክል የዘለቀው ተቃውሞ በጨዋታው ኮሚሽነር ጥረት ሊቀጥል ችሏል። በተለያዩ ምክንያቶች በየጨዋታዎቹ መሐል መቆራረጦች የተለመዱበት ሊጉ ይህን መሰል መቋረጥ ሲያስተናግድ በዚህ ዓመት የመጀመርያው ነው።

👉 ከሜዳ ውጭ ደካማው ፋሲል

አየዐምና የሊጉን ክብር ለመጎናፀፍ ከጫፍ ደርሰው የነበሩት ፋሲሎች ዘንድሮው ዐምና ለጥቂት ያጡትን ዋንጫ እንዲያሳኩ በክለቡ ዙሪያ ባሉ አካላት ዘንድሮም ቢሆን ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ነገርግን ቡድኑ ለዋንጫ እንደመጫወቱ አሁንም ከመሪዎቹ ያለው ርቀት ጠባብ የሚባል ቢሆንም ቡድኑ በተለይ በሜዳው ላይ ያለውን ጥንካሬ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጨዋታዎች መድገም የግድ ይለዋል። ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ ብርቅ በሆነበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሌሎቹ ክለቦች ነጥሮ ለመውጣት ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች የሚገኙ ነጥቦች በሊጉ ፍፃሜ እጅጉን ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ይሆናል።

ዘንድሮ እንኳን በሊጉ ካደረጋቸው 5 የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች እስካሁን ምንም ማሸነፍ አልቻለም። ከወላይታ ድቻ፣ ሰበታ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ በወልቂጤ ከተማ እና ስሑል ሽረ ሽንፈትን አስተናግደዋል።

👉 የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች የሥነምግባር ጉዳይ

በ9ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በኢትዮጵያ ቡና 2-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ የዕለቱ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሀብታሙ ታደሰ ላይ ግርማ በቀለ ጥፋት ሰርቷል በሚል የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ተከትሎ እጅግ አነጋጋሪ የነበሩ ክዋኔዎች ታይተዋል።

የመስመር ተከላካዩ ተስፉ ኤልያስ የመጫወቻ ኳሱን ወደ ተመልካች የመታበት ሂደት የቡድኑ ተጫዋቾች ዳኛውን ሲያዋክቡና ሲገፈታትሩ የነበረበት ይባስ ብለው እስከ መተናነቅ የደረሱበት ክስተት፤ ዮሴፍ ዮሐንስ ቢጫ ካርድ ሲመለከት “በስላቅ” ዳኛውን እየተከተለ ሲያጨበጭብበት የነበረው ሁኔታ፤ በተቀሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ቀሪ ሰከንዶች የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ከፍተኛ ኃይልን ቀላቅለው የተጫወቱበት መንገድ ከብዙ በጥቂቱ በጨዋታው የነበረው ያልተገባ ድርጊቶች ውስጥ ከብዙ በጥቂቱ ለማሳያነት የቀረቡ ናቸው።

የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ እንደ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች በዳግም ምልሰት ታይቶ ውሳኔ በማይቀለበስበት ሊግ በዳኛ የተወሰነን ውሳኔ በፀጋ ከመቀበል ውጭ ያለ አማራጭ ራስንና ቡድን ከመጉዳት በዘለለ የሚያስገኘው ውጤት በሌለበት መሰል የዳኛ ከበበና ማዋከቦች ስለምን አስፈለጉ የሚለው መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው። ለማሳያነትን በዚህኛው ሳምንት የሆነውን አነሳን እንጂ በሌሎች ሜዳዎችና ጨዋታዎች ላይ የሚሆኑትን ደግሞ ማሰብ ጉዳዩን ምን ያህል ስር የሰደደ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል።

👉 አግብቶ የሚገባበት ባህርዳር ከተማ

ዘንድሮ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሰር ከቀደመው ጥንቃቄ መር አጨዋወት ተላቀው ወደ አዎንታዊ አጨዋወት በመሸጋገር ላይ ያለው ባህር ዳር ከተማዎች ከዓምናው በተለየ ግቦችን ለማስቆጠር የማይቸገር ነገርግን ግቦችን በቀላሉ የሚያስተናግድ ቡድን እየሆነ መጥቷል።

በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች የአዳማ ሲሶኮ አጣማሪ አለመገኘት ፣ የመሐል ተከላካዮች ቀርፋፋነትና መሰል ችግሮች የመከላከል አደረጃጀቱን በእንከኖች የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል። ለማሳያነትም እስካሁን ባደረጋቸው ሁሉም ጨዋታዎች ከአንድ መርሐ ግብር በስተቀር ቡድኑ ግብ ያስተናገደ ሲሆን በተለይም ከፋሲል፣ ሀዲያ፣ መቐለ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ከወልዋሎ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁለትና ከዚያ በላይ ግቦችን አስተናግዷል።

ስለዚህም ቡድኑ ወደ ተሻለ የውጤታማነት መንገድ እንዲያመራ ግቦችን ከማስቆጠር በዘለለ የሚያስተናግዳቸውን የግብ መጠኖች መቀነስ ይኖርበታል። በተለይም ጎሎች ካስቆጠረ በኋላ በፍጥነት መሪነቱን ለማስጠበቅ የሚወሰዱ ዝግጅት ያልተደረገባቸው እርምጃዎችን መቀነስ ይኖርባቸዋል።

👉 ያለ በቂ ልምምድ ጨዋታ ያደረገው አዳማ ከተማ

ደሞዝ ካልተከፈለን አንጫወትም በሚል ያለፉትን ቀናት ልምምድ አቁመው የነበሩት አዳማ ከተማዎች በስተመጨረሻም ወደ ድሬዳዋ አምርተው በድሬዳዋ 2-1 ተሸንፈው ተመልሰዋል። የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ድሬዳዋ ለማምራት የወሰኑት በ11ኛው ሰዓት ሲሆን በጨዋታው ዋዜማ ቀላል ልምምድ ከመስራት በዘለለ በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ቡድኑ በጨዋታው መጀመርያ ሁለቱንም ጎሎች ማስተናገዱ በቂ ልምምድ ያለማድረግ ውጤት እንደሆነ የሚያሳብቅ ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት በመግባት ልዩነቱን ከማጥበብ አልፈው ጥሩ መንቀሳቀስ ችለው ነበር።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በ7ኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋሮች ልምምድ ሳይሰሩ ከአዳማ ከተማ 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት መለያየታቸው የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ