ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፪) | ተጫዋች ትኩረት

በ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በርካታ ተጫዋቾች የትኩረት ማዕከል መሆን ችለዋል። እኛም ዋና ዋናዎቹን መርጠን በተከታዩ መልኩ አሰናድተናል።

👉 ኦኪኪ ኦፎላቢ በስተመጨረሻም ግብ አስቆጥሯል

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ኦኪኪ በክረምቱ ወደ መቐለ ካመራ ወዲህ ለክለቡ ባደረጋቸው የነጥብ ጨዋታዎች ላይ እስከ ትላንት ድረስ ግብ ማስቆጠር አልቻለም ነበር። ተጫዋቹ በትላንትናው ዕለት ሰበታ ከተማን 2-1 ሲረቱ ሁለቱንም የማሸነፊያ ግቦች በማስቆጠር በአዲሱ ቡድኑ የግብ አካውንቱን በማይረሳ መልኩ መክፈት ችሏል።

በቅጣት ምክንያት በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ያልተሰለፈው ናይጄርያዊው አጥቂ ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላ ከቡድኑ ጋር ለመዋሀድ ተቸግሮ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹን በአግባቡ የሚያውቁት አሰልጣኝ ገብረመድህን ምርጥ ብቃቱን አውጥቶ የሚጠቀምበትን ቀመር ያገኙ ይመስላሉ። በ4-4-2 የመጨረሻ አጥቂ የሆነው ኦኪኪ ከአማኑኤል ጋር የፈጠረው መናበብ ለአማኑኤልም ሆነ ለክለቡ ጥቅም እያስገኘ ሲሆን አሁን ደግሞ ራሱም ምቾት እየተሰማው እንደመጣ ጎል በማስቆጠር አሳይቷል።

ትጉህ አይደለም በሚል ከሰሞኑ ጫናዎች በርከተውበት የነበረው የ2010 የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ኦኪኪ በትላንትናዎቹ ሁለት ግቦች በመታገዝ የቀደመውን ስልነቱን ያሳየን ይሆን?

👉 ዕድሉን በአግባቡ የተጠቀመው ሀብታሙ ታደሰ

በካሣዬ አራጌ ስር በአዲስ የጨዋታ ሀሳብ እንደ አዲስ እየተዋቀረ በሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከሰሞኑ የቡድኑ ምርጡ ተጫዋች እሱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቡና በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕናን 5-0 ሲረታ ተቀይሮ በመግባት የማሳረጊያ ግብ በአስደናቂ አጨራረስ በማስቆጠር ራሱን ለደጋፊው ያስተዋወቀው ሀብታሙ በባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ቡድኑ ቢሸነፍም ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር አንድ ግብ አስቆጥሮ ሌላ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ የሰጠ ሲሆን በትላንቱ ጨዋታ ደግሞ ከአስደማሚ ብቃት ጋር ለአንዷ ግብ መቆጠር ምክንያት ሲሆን ሌላኛውን ደግሞ እራሱ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ እና በሊጉ ጅማሮ እጅግ ውስን የሆኑ የጨዋታ ደቂቃዎችን ያገኘው ሀብታሙ አሁን ላይ በአጥቂ ተጫዋቾች ጉዳት ያገኛቸውን ዕድሎች በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል። ይህም ለአሰልጣኝ ካሣዬ ፊት መስመር ላይ ጥሩ የተጫዋቾች ፉክክር የሚፈጥርላቸው ሲሆን ሀብታሙ በሰሞነኛ ብቃቱ የሚቀጥል ከሆነ ቦታውን የግሉ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

👉 ትንሹ ብሩክ ሀዋሳን በጫንቃው መሸከሙን ቀጥሏል

ብሩክ በየነ በሚንገራገጨው የሀዋሳ ከተማ የሊጉ ጉዞ ቡድኑን አሁንም ተሸክሞ መውጣቱን ቀጥሏል።

ገና የከፍተኛ ደረጃ እግርኳስ ጅማሮው ላይ የሚገኘው ብሩክ ትናንት ሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ቡድኑን በገጠመበት የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ ሁለት ግቦችን የቀድሞ ክለቡ ላይ በማስቆጠር አሁንም ለሀይቆቹ አለኝታ መሆኑን አሳይቷል። በአጠቃላይ የ9 ሳምንት የሊጉ ጉዞ 6 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነት ደረጃ በ2ኛነት ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር በመሆን እየተከተለ የሚገኘው ተጫዋቹ ብሩህ ዓመታት ከፊቱ እንደሚጠብቁት እያሳየ ይገኛል።

ብሩክ ጥሩ ባልሆነባቸው ጨዋታዎች ነጥብ ይዞ ለመውጣት የሚቸገረው ሀዋሳ በቀጣይ በሊጉ የተሻለ ጉዞን ለማድረግ የብሩክ በተሻለ ብቃት ላይ መገኘትን የሚጠብቅ ይመስላል።

👉 የእንዳለ ዘውገ ጎል

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያድጉ ቡድኖች በቅድመ ዝግጅት ወቅት በሚያደርጉት የተጫዋቾች ጅምላ ቅየራ ቡድኖቻቸው ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተጫዋቾችን በብዛት ሲለቁ ከቆዩም ደግሞ በተጠባባቂነት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ማየት የተለመደ ነው።

በሰበታ ከተማ ውስጥ ዐምና ጥሩ ግልጋሎት ሲስጥ የነበረው እንዳለ ዘንድሮ ምንም እንኳን በአመዛኙ በተጠባባቂነት ቢያሳልፈም ቡድኑ በመቐለ ሲሸነፍ ወደ ሜዳ ተቀይሮ በመግባት ጎል አስቆጥሯል። በዚህች ግብ እንዳለ ዘውገ ወደ ሊጉ አዲስ ካደጉ ቡድኖች ውስጥ ከቡድኑ ጋር አብረው ካደጉ ተጫዋቾች የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች መሆን ችሏል።

እንዳለ ግብ ማስቆጠሩ ለሌሎች ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለተሸጋገሩ ተጫዋቾች ተስፋን የሚፈነጥቅ ሊሆን ይችላል።

👉 ምንተስኖት አሎ

ከሊጉ ምርጥ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል የሚጠቀሰው ምንተስኖት አሎ ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎች እድል ማግኘት አለባቸው ብለው ለሚሞግቱ የስፖርት ቤተሰቦች ጥሩ ምሳሌ እየሆነ ይገኛል። ስሑል ሽረን ዘንድሮ የተቀላቀለው ምንተስኖት አጀማመሩ ላይ ቢቸገርም ከፊቱ ከሚሰለፉት ተከላካዮች ጋር በፈጠረው አስደናቂ መናበብ ያለፉትን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ መውጣት ችሏል።

ይህ ዕውነታ ለውጤታማነቱ የኋላ ክፍሉ ላይ አብዝቶ የሚተማመነው የአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ስብስብን አድናቆት እንድንቸረው የሚያደርግ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ