ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፫) | አሰልጣኞች ትኩረት

በ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የተከሰቱ ሁነቶችን ከአሰልጣኞች አንፃር ቃኝተን እንዲህ ተመልክተነዋል።


👉 አስገዳጅ ደንብ የሚያስፈልገው ድህረ ጨዋታ አስተያየት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተሻሻሉ ነገሮች መካከል የአሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ አስተያየት መስጠት መበራከቱ ነው። ሆኖም ይህ ጉዳይ በአሰልጣኞቹ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ወጥ እንዳይሆን እያደረገ ይገኛል። ክለባቸው ሲያሸንፍ ከካሜራ ነና መቅረፀ ድምፅ ፊት ቀድመው የሚገኙት አሰችጣኞች ሽንፈት ሲያጋጥማቸው ከአካባቢው መሰወር እና መግለጫ ላለመስጠት ፈቃደኝነታቸውን ሲነፍጉ በተደጋጋሚ እየተስተዋመለም ይገኛል። በዚህ ሳምንትም የጅማ አባ ጅፋር፣ ወልዋሎ እና አዳማ ከተማ አሰልጣኞች የዚህ ሁኔታ ገላጭ ነበሩ።

አወዳዳሪው አካል በውድድሩ ላይ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የሆነውን የአሰልጣኞች አስተያየት የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ወደ አስገዳጅ ደንብነት ቢያሸጋግር የመጀመርያዎቹ ተጠቃሚዎች በድልም ሆነ በሽንፈት ውስጥ ሀሳቦቻቸውን እንዲገልፁ፣ ምክንያታዊነትን እንዲያዳብሩ፣ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር መልካም ግንኙነት እንዲፈጥሩ፣ በስፖርት አፍቃሪው እንዲታወቁ እንዲሁም እግርኳሳዊ ሀሳቦቻቸው በቀጣሪ አካላት ግምት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ተጠቃሚ የሚያደርገው ራሳቸው አሰልጣኞችን እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል።

ከአሉታዊ ገፅታዎች ባሻገር ቡድናቸው የትኛውንም ውጤት ቢያስመዘግብ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሰልጣኞች ደግሞ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው። በዚህ ሳምንትም ዘርዓይ ሙሉ፣ ውበቱ አባተ እና ደግአረግ ይግዛው ቡድናቸው ሽንፈት አስተናግዶ ድሕረ ጨዋታ አስተያየታቸውን መስጠታቸውን መጥቀስ ይቻላል።

👉 ሀዋሳ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ድቻ

በተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ርቆ የቆየው ሀዋሳ ከተማ በዚህ ሳምንት ድል ማስመዝገባቸው ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለአሰልጣኝ አዲሴ ካሳም እፎይታን ፈጥሮላቸዋል። አሰልጣኙ በአምስት ጨዋታዎች ከድል ርቀው የነበረ እንደመሆኑ በዚህ ጨዋታ ሽንፈት ቢያስተናግዱ መንበራቸው መነቃነቁ አይቀሬ ነበር።

በሀዋሳ ሽንፈት ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማ የሊጉን ግርጌ መያዙ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛውን ጫና ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው። ለሊጉ አዲስ የሆኑት አሰልጣኝ ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን እየገነቡ እንደመሆኑ ጊዜ ቢያስፈልጋቸውም ቡድኑን ከሥጋት ነፃ ቦታ ላይ የማስቀመጥ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።

አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ወላይታ ድቻን በጊዜያዊነት ተረክበው በመጀመርያ ጨዋታቸው ያልተጠበቀ የሜዳ ውጪ ድል ከሜዳቸው ውጪ ማሳካት ችለዋል። አሰልጣኙ ቡድኑን ከተረከቡ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደመሆናቸው ከመሰረታዊ ለውጦች ይልቅ የተጫዋቾችን ተነሳሽነት በመጨመር ወደ ሜዳ ማስገባታቸው ለድላቸው አስተዋፅኦ ማድረጉ እሙን ነው። አሰልጣኙ በድሕረ አስተያየታቸው የተናገሩትም ይህንኑ ነበር።

ዐምናም በተመሳሳይ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የመጀመርያ ጨዋታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን የረቱት አሰልጣኙ የቡድኑን ተነሳሽነት በማስቀጠል ከመጥፎ አጀማመሩ ማገገሙን እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

👉 ዋና ዋና ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች 

* ከሽንፈት መልስ ለሽንፈቱ ውጫዊ ተፅዕኖዎችን በምክንያትነት ማቅረብ ልምዳቸው እያደረጉ የመጡት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት በኋላ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ጨዋታው ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር ፤ በጨዋታው ደስተኛ ብሆንም በዳኝነቱ ግን አይደለሁም። የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ሆነ ለሁለተኛው ጎል ምክንያት የሆነው የማእዘን ምትም ጭምር በዳኝነት ስህተት የተሰጡብን ናቸው።ይህ ደግሞ የተጫዋቾችን ስነ ልቦና ያወርዳል በተለይ ከሁለተኛው ጎል በኃላ እነሱ የተሻሉ ናቸው ምክንያቱ ደግሞ የኛ ልጆች በስነልቦናው ረገድ መውረዳቸው ነው።”

*የመቐለው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከግብ ማስቆጠር ርቆ ስለነበረው ኦኪኪ ይህን ብለዋል

“ኦኪኪ ከግብ ርቆ ስለነበር እንደ አጥቂ ትንሽ መረበሾች ነበሩት።ዛሬ ግን ከሁለት በላምይ ማግባት ይችል ነበር ፤ ወደ ግብ ማግባት መመለሱም በቀጣይ የማጥቃት ሀይልችን በተሻለ ያጠናክርልናል።”

*የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ ስለ ሆሳዕና የመጫወቻ ሜዳና ስላልተለመደው የአስቻለው ታመነ ሚና

“የምትፈልገውን ማድረግ በማትችልበት በዚህ ሜዳ መጫወት በጣም ይከብዳል። ምንም ማድረግ አልቻልንም ፤ ከዚህም ሜዳ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች ሜዳዎችም ብመለከትም ይህ ትንሽ ይከብዳል።”

“አስቻለው በቡድኔ ውስጥም በብሔራዊ ቡድንም በተከላካይነት ተጫውቷል። ነገርግን በጣም አቅም ያለው፣ በግንባር የሚገጭ፣ ጉልበት ያለው ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ሁለገብ ተጫዋች ነው። ዛሬም አማካይ ሆኖ በመጫወት ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ