“በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገብነውን ውጤት ማሻሻል እንፈልጋለን” አንድሪው ጅያን ሊዊ

ሴንት ሚሸል ዩናይትድ ቅዱስ ጊዮርጊስን በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ 10፡00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይገጥማል፡፡ የሴንት ሚሸል ዩናይትድ አሰልጣኝ አንድሪው ጅያን ሊዊ የአዲስ አበባ የዓይር ፀባይ የሚፈልጉትን ዓይነት የጨዋታ ስልት እንዳይጠቀሙ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ለሲሸልስ ዕለታዊ ጋዜጣ ቱደይ ኢን ሲሸልስ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ ጅያን ሊዊ የሲሸልስ እግርኳስ ፌድሬሽን ጨዋታ ከመደረጉ ከስድስት ቀናት በፊት እንዲመጡ ነገሮችን ቢያመቻች ኖሮ ተጠቃሚ ይሆኑ እንደነበር ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“በሁለት ቀናት ውስጥ የዓይር ፀባዩን መልመድ ያስቸግራል፡፡ የጨዋታ ስልታችንን ያበላሽብናል ምክንያቱም አጥቅተን መጫወት ስለሚቸግር፡፡ ስለዚህ ትግስት ሊኖረን እና ጉልበታችንን ልንቆጥብ ይገባል፡፡”

አሰልጣኙ አክለው 18 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ቡና የደረሰባቸውን የ8-1 ሰፊ ሽንፈት ማሻሻል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

“ጥሩ ዝግጅት ነበር ያደረግነው፡፡ በዝግጅት ወቅት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለናል፡፡ ምንም እንኳን የጨዋታዎቹ ክብደት ቢለያይም፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተጫውተን እናውቃለን፡፡ የኛ ፍላጎት ካለፈው የኢትዮጵያ ጉብኝታችን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ነው፡፡ ዓምና ከጠንካራው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር የተሻለ መጫወት ችለን ነበር፡፡ በጋራ ተጫውተን በጣባብ ውጤት አሸንፎ ውይም አቻ ውጤት ይዞ መመለስን አቅደናል፡፡”
ሴንት ሚሸል የ2015 የሲሸልስ ባርክሌስ ፕሪምየር ሊግ ከተጠናቀቀ በኃላ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ክለቡ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ጨዋታዎች ሽንፈትን አላስተናገደም፡፡ ለዕረፍት ወደ እንግሊዝ አቅንቶ የነበረው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ካርል ሃል ቡድኑን መቀላቀሉ ለአሰልጣኝ ጅያን ሊዊ ደስታን ፈጥሯል፡፡ ሃል የ2015 የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ነበር፡፡ ቀለል ያለ ጉዳት ያጋጠመው አጥቂው ጀርቪያስ ዌይ ሃይቭ ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው እነደሚደርስ ተጠብቋል፡፡

12705347_1121960797817094_7129668729216048421_n
ሴንት ሚሸል ዩናይትድ በ2015 የውድድር ዘመን 29 ጨዋታዎችን ሲያደርግ በ20 ጨዋታዎች ድል ተገዳጅቷል፡፡ 3 ጨዋታ አቻ ሲወጣ በስድስቱ ሽንፈትን ቀምሷል፡፡ ባጠቃላይ ክለቡ በተወዳደረባቸው ውድድሮች ላይ 97 ግቦችን አስቆጥሮ 36 ግቦችን ደግሞ በአንፃሩ ተቆጥረውበታል፡፡ ክለቡ የሊጉን እና የፕሬዝደንትስ ዋንጫ ያነሳ ሲሆን የኤርቴል ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ ነበር፡፡

ፎቶ ምንጭ – የሴንት ሚሸል የፌስቡክ ገፅ

ያጋሩ