ግብጻዊው የተጫዋቾች ወኪል የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ለመስራት አቅዷል

Read Time:1 Minute, 44 Second

ከኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያለው ወኪል ነው። ባለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ወደ ግብፅ ክለቦች ላደረጓቸው ዝውውሮችም ወሳኙን ሚና ሲጫወት የቆየ ግለሰብ ነው። ግብፃዊው የእግርኳስ ተጫዋቾች ወኪል አብዱራህማን መግዲ!

ወኪሉ በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያ ተገኝቶ የነበረ ሲሆን ስለ ጉብኝቱ፣ ስለ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ስላለው እቅድ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ስለ ኢትዮጵያ ጉብኝቱ

“አሁን በኢትዮጵያ የተገኘሁት በበርካታ የግል እና የሥራ ጉዳዮች ምክንያት ነው። ከነዚህ ጉዳዮችም አንዱ እና ዋነኛው አንድ የቡርኪ ፋሶ ዜጋ ተጫዋች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ነው። እግረ መንገዴንም በኢትዮጵያ የሚገኙ ወዳጆቼን ለማግኘት እና በሀገራችሁ እግርኳስ ያለውን የሥራ ዕድል ለማየት ችያለሁ።

“ለወደፊቱ በእኔ ውክልና ያላቸውን ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለማምጣት ማሰብ ጀምሬያለሁ። የሊጉ የእግርኳስ ደረጃ መጥፎ አይደለም፤ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው የሚከፍሉት ገንዘብም ጥሩ ነው። ከኢትዮጵያ ክለቦች ጋር በጋራ የማልሰራበት ምክንያት አይታየኝም።”

ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ላይ ትኩረቱን ስለማድረጉ

“እውነት ነው፤ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ላይ ትኩረት አድርጌ እሰራለሁ። ይህም የጀመረው አስቤበት ሳይሆን በአጋጣሚ ነው። ከሳላህዲን ሰዒድ ጋር በግብፁ ዋዲ ደግላ በሚጫወትበት ጊዜ ተዋውቀን የእርሱ ወኪል ሆንኩኝ። በዚህም ምክንያት ሳላህዲን የሚጫወትባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች መመልከት ጀመርኩ። እነ ሽመልስ፣ ዑመድ፣ በኋላም ጋቶች በብሔራዊ ቡድኑ በሚያሳዩት አቋም ደስተኛ ስለነበርኩ አብሬያቸው ለመስራት ፈቅጄ፤ ነገሮችም ተሳክተውልን በግብፅ እየተጫወቱ ይገኛሉ። ከሦስቱ ተጫዋቾች ውጪም ሌሎች የብሔራዊ ቡድኑ ተሰላፊዎችንም ወደ ግብፅ ክለቦች ለመውሰድ ጥረት አድርጌ ሳይሳካ የቀረበት አጋጣሚም ነበር። ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጋር የሚሰሩ ብዙ ዓለምአቀፍ ወኪሎች እንደሌሉ ስለታዘብኩ በሃገራችሁ ላይ ትኩረት አድርጌ ለመስራት ወስኛለሁ።”

በቀጣይ ወደ ግብፅ ለመውሰድ ያቀዳቸው ተጫዋቾች

“አሁን የምናገረው የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም እንደ ቢንያም በላይ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ያሉ ተጫዋቾች አድናቂ ነኝ። ከዚህ ቀደም የግብፅ ክለቦች በሁለቱም ተጫዋቾች ላይ ፍላጎታቸውን ያሳዩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ዝውውሮቹን ማጠናቀቅ ሳንችል ቀርተናል።”

በኢትዮጵያ ስለሚከፍተው አካዳሚ

“በኢትዮጵያ አንድ የእግርኳስ አካዳሚ ለመመስረት አቅጃለሁ። አካዳሚው በአውሮፓውያን የእግርኳስ ፅንሰ-ሐሳብ የተገራ እና ከአውሮፓ በሚመጡ የእግርኳስ ባለሞያዎች የሚመራ ይሆናል። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎችም በአካዳሚው የሚሰሩ ይሆናል፤ ይህም የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ ባለሞያዎች ስብጥር ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትክክለኛ የሆነ የስልጠና መርሃግብር እንድንነድፍ ይረዳናል ብዬ አስባለሁ። ይህንን የማሰልጠኛ ተቋም በኢትዮጵያ ለመክፈት ያነሳሳኝም በሃገሪቱ እስካሁን ድረስ ተመሳሳይ ጠንካራ አካዳሚዎች አለመኖራቸውን በማየቴ እና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼም ለፕሮጀክቱ መሳካት የተቻላቸውን ድጋፍ ያደርጉልኛል ብዬ ስለማምን ነው። የአካዳሚው የመጀመሪያ ቅርንጫፍ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ የሚከፈት ሲሆን በቀጣይ ወደ ክልል ከተሞችም የማስፋት ዕቅድ ይዣለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!