ታህሳስ 24 የመኪና አደጋ የደረሰባቸው የአዴት ከተማ ተጫዋቾች ወደ መልካም ጤንነት ላይ እየተመለሱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በአማራ ሊግ የሚሳተፉት አዴት ከተማዎች ታህሳስ 25 ላለባቸው የምድብ የመክፈቻ ጨዋታ ጉዞ ሲያደርጉ የመኪና አደጋ እንደደረሰባቸው ይታወቃል። ሶከር ኢትዮጵያም በሰዓቱ ቡድኑ ከአይከል ወደ ገንደ ውሃ ሲጓዝ በተፈጠረ የመኪና መገልበጥ አደጋ 7 የቡድኑ አባላት ከፍተኛ አደጋ አጋጥሟቸው ወደ ጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል እንደተወሰዱ እና ቀሪዎቹ አባላት ደግሞ መጠነኛ አደጋ እንዳጋጠማቸው መዘገቧ ይታወሳል።
ዛሬ የአዴት ከተማ ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ዓለምነህ ይትባረክ አደጋ ስለደረሰባቸው ተጨዋቾች ወቅታዊ ሁኔታ ጥያቄ አቅርበንላቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።” በሰዓቱ አደጋ ካጋጠመን ውስጥ 7 ሰዎች ወደ ጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና ተወስደው ነበር። እኔን ጨምሮ ሌሎች በመኪና ውስጥ የነበርን አባላት ቀላል አደጋ ስለደረሰብን በጭልጋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመጀመሪያ ህክምና ተደርጎልን ወደ አዴት ከተማ ሆስፒታል መጥተናል። ወደ ጎንደር ከተላኩት 7 ሰዎች ውስጥ ደግሞ አምስቱ እንደእኛ ወደ አዴት ከተማ ተመልሰው በተመላላሽ ህክምና ክትትል እያደረጉ ነው። ነገር ግን 2 ተጫዋቾች ከፍተኛ አደጋ ስለደረሰባቸው ለቀናት በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ተኝተው ክትትል አድርገዋል። ከአምስት ቀናት በፊት ደግሞ አንደኛው ተጨዋች (አብርሃም መንበር) መጠነኛ የጤና መሻሻል ስላሳየ ከሆስፒታሉ እንዲወጣ ተደርጓል።” ብለዋል። አቶ ዓለምነህ ጨምረውም ጠበቃው አልማው የተባለ የቡድኑ ተጨዋች እስካሁን ከሆስፒታል እንዳልወጣ ገልፀዋል።
የቡድን መሪው በሃሳባቸው መገባደጃ ላይ ይህንን ብለዋል።” በአደጋው የስፖርተኛው የግል እና የጋራ ንብረቶች በጠቅላላ ወድመዋል። ከታኬታ ጀምሮ ያሉ ንብረቶቻችንን እንዲተካልን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እያደረግን ነው። ከዚህ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩም የሞራል ካሳ አልሰጠንም። ስለዚህ እነዚህ ሁለት ነገሮች እንዲስተካከሉልን ንግግሮችን እያደረግን ነው።”
በአማራ ሊግ የሚወዳደረው ክለቡ በዚህ ዓመት በሚሳተፍበት ሊግ ውድድር እንደማያደርግ ነገር ግን ከሊጉ በቀጣይ ዓመት እንዲወርድ እንዳይደረግ የአማራ እግር ኳስ ፌደሬሽን ትብብር እንዲያደርግለት የከተማ አስተዳደሩ ደብዳቤ እንደፃፈ እና ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነ ታውቋል። የፌደሬሽኑ ምላሽ ምንም ይሁን ምንም ግን ተጫዋቾቹ ከደረሰባቸው አካላዊ እና አዕምሮአዊ ስብራት ሙሉ ለሙሉ ስላላገገሙ ቡድኑ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንደማይሆን ተጠቁሟል።
© ሶከር ኢትዮጵያ