ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተጫዋቾች ጨዋታ አድርገው ወደ መቐለ በሚመለሱበት ወቅት ባልታወቁ ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ከባድ ጉዳት ደርሶበት የነበረውና ከበድ ያለ የመተንፈሻ ቀዶ ጥገና ያደረገው ኤፍሬም ኪሮስ ከከባዱ ጉዳት በማገገም ወደ ሜዳ ተመልሶ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች አስቆጥሯል።
ወደ እግር ኳስ ለመመለስ ይቅርና በሕይወት ለመቆየትም ከባድ የሆነ ጉዳት የደረሰበት ይህ ተጫዋች ስለ ሁኔታው እና ወቅታዊ አቋሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።
ጥቃቱ በደረሰባቸው ወቅት ስለነበረው ሁኔታ
በአድካሚ ጉዞ ላይ ነበርን። ድንገት ነው የጥይት እሩምታ የሰማነው። እኔም ቆይቼ ነው መመታቴን ያየሁት። ከሁኔታው በኋላ ህዝቡ ጥሩ ትብብር ባያደርግልን በሕይወት የመቆየቴ ነገርም ጥያቄ ውስጥ ነበር።
ስለ ጉዳቱ እና በህክምና ስላሳለፋቸው ወራት
በጣም ከባድ ወቅቶች ነበሩ። ድጋሚ ወደ እግር ኳስ እመለሳለው ብዬ አላሰብኩም። ጉዳቱ ከባድ ስለነበር ወደ አንድ ወር የሚጠጋ ነው በሆስፒታል የቆየሁት። በተለይም የገባብኝ ጥይት እስኪወጣ የነበረው ግየጊዜ በጣም ከባድ ነበር። ከህክምና ከወጣሁም በኃላ ወደ መደበኛው አተነፋፈስ ለመምጣት ተቸግሬ ነበር።
ስለ ወቅታዊ ሁኔታው
ከረጅም ጊዜ በኃላ (በአንደኛ ሊግ ውድድር) ከአራዳ ክፍለከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በቋሚነት ጀምሬ በጨዋታው ሁለት ግቦች አግብቻለው። በሁለተኛው ከፈራውን ጋር በነበረው ጨዋታም አንድ ግብ አግብቻለው። ፈጣሪ ይመስገን ወደ ሙሉ ጤንነቴ ተመልሼ በጥሩ ብቃት ላይ እገኛለው። በጉዳት ወቅት ከጎኔ ለነበሩት ሁሉም ማመስገን እፈልጋለው። ክለቤ ዋልታ ፖሊስ ትግራይ በብዙ ረገድ አግዞኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ