ቅዱስ ጊዮርጊስ ሴንት ሚሼልን በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቷል

 

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የሲሸልሱን ሴንት ሚሼል ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸንፏል፡፡

በ16ኛው ደቂቃ ራምኬል የሴንት ሚሼል ተከላካዮችን የጨዋታ ውጪ ወጥመድ ጥሶ ለአዳነ ግርማ ያሻገረለትን ኳስ አዳነ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹ 1-0 እንዲመሩ አስችሏል፡፡ ከግቡ በኋላ መቀዛቀዝ ያሳየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በራምኬል ሎክ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ የማስቆጠር አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ፈረሰኞቹ ወደ እረፍት ከማምራታቸው በፊት 2ኛውን ግብ በ43ኛው ደቂቃ አዳነ ከረጅም ርቀት የተሸገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ለበኃይሉ ያቀበለውን ኳስ የመስመር አማካዩ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡

ከእረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ የግብ እድሎችን እንደሚፈጥሩ እና ግቦችን እንደሚያስቆጥሩ ቢገመትም ከግምቶች በተቃራኒው የተቀዛቀዘ እና ለአጥቂዎች በረጅሙ ኳሶችን በማድረስ አሳልፈዋል፡፡ ከወር በፊት ለፈረሰኞቹ ፊርማውን ያኖረው ጎድዊን ቺካ በሁለተኛ አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታውን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያደርግ በ80ኛው ደቂቃም የቅዱስ ጊዮርጊስን የማሳረግያ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲካሄድ  በዩኒቲ ስታድየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ያጋሩ