የፊፋ ተወካዮች ከሰሞኑ አዲስ አበባ ይመጣሉ

የፊፋ ተወካዮች ከ10 ቀናት በኋላ የተለያዩ ጉዳዮችን ለመፈፀም አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡

ኢትዮጵያ በያዝነው ዓመት ክረምት ዓለም አቀፉን የፊፋ አባል ሀገራት ስብስባ (ኮንግረንስ) በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ታሰናዳለች፡፡ ይህ ስብሰባ የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊ ጉዳዮችን ለሁለት ጊዜያት ተወካይ በመላክ ሲመለከት የነበረው ፊፋ አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ግምገማውን ከማድረግ ባሻገር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር በሌሎች ተዛማች የመሠረተ ልማት ጉዳዮችን ውይይት ለማድረግ ጥር 25 ሰኞ ዕለት ሁለት ባለሙያዎች ወደ ሀገራችን እንደሚመጡ አቶ ኢሳይያስ ጅራ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ የፊፋ ሰዎች ስለሚመጡበት ምክንያት ሲናገሩ ” በኮንግረሱ ያስፈልጋሉ ተብለው ስንዘጋጅባቸው የነበሩትን ቅድመ ዝግጅቶች ለመመልከት እንዲሁም አጠቃላይ ዕቅዶች በፌዴሬሽኑ ሰዎች ለተወካዮቹ ማቅረብ ዋና ጉዳዮች ሲሆኑ በአዲስ አበባ ያለው የፊፋ አካዳሚ መመልከትን እና ያስፈልጉታል የሚባሉትን ጉድለቶች ተመልክቶ መፍትሔ ለማበጀትም ጭምር ይመጣሉ።” ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በርካታ የዓለማችን የእግርኳስ መሪዎች ወደ ሀገራችን ለጉባዔው የሚመጡ በመሆኑ ከኢሚግሬሽን ጋር በመነጋገር ነፃ ቪዛ መንግሥት እንዲያመቻች ለመጠየቅ በሚያስችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ይመጣሉ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ይህ ጉብኝት ካለፉት ጊዜያት አንፃር የተለየ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የመጨረሻ የግምገማ ምዕራፍ መሆኑንም ሰምተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ