ቅድመ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ጅማ አባጅፋር

ስሑል ሽረዎች ጅማ አባጅፋርን በትግራይ ስቴድየም የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በድንቅ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት እና ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አሸንፈው ወደ ሊጉ አናት የተጠጉት ስሑል ሽረዎች ጥሩ ጉዟቸው ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ

 

ባለፉት ጨዋታዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ያልተቸገሩት ስሑል ሽረዎች በነገው ዕለትም መልሶ ማጥቃት የመጀመርያ ምርጫቸው አድርገው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ጅማ አባ ጅፋር ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ጠጣር ቡድን እንደ መሆኑ ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ጅማ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በራሱ የሜዳ አጋማሽ ተገድቦ የሚጫወት ቡድን መሆኑ በቂ ክፍተት እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል።

በዚህም ባለፉት ሳምንታት ተመሳሳይ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድኑ የሚያጠቃትበት መንገድ ላይ ለውጦች ማድረግ የግድ ይለዋል። ምንም እንኳ ሳምሶን አየለ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወታቸው ይቀይራሉ ተብሎ ባይገመትም አሰልጣኙ በጨዋታው ሂደት ላይ የአጨዋወት ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።

ስሑል ሽረዎች በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ሆኖም ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ በግል ጉዳይ በዚ ጨዋታ አይሰለፍም።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ

ባለፈው ሳምንት በወላይታ ድቻ በሜዳቸው ሽንፈት የገጠማቸው ጅማ አባ ጅፋሮች ሦስተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዶ ወደ ወራጅ ቀጠናው ላለመውረድ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።
ጥሩ የመከላከል አደራጀት ያላቸው ጅማ አባ ጅፋሮች የጎል ዕድል በመፍጠር ረገድ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎች ቢያሳዩም አሁንም ችግሩን መቅረፍ አልቻሉም። በተለይም ቡድኑ ሁነኛ የፊት አጥቂ ተሰላፊ አለመያዙ የግብ ማስቆጠር ችግሩ ትልቅ አድርጎታል። ሆኖም ቡድኑ በስራ ፍቃድ ምክንያት ካጣቸው ተጫዋቾች መካከል አጥቂው ያኩቡ መሐመድ መጠቀም መጀመሩ የግብ ማስቆጥር ችግሩ በተወሰነ መልኩ ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

ጅማ አባጅፋሮች ሄኖክ ገምቴሳን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ብሩክ ገብረአብ እና ብዙዓየሁ እንደሻው በጉዳት ወደ መቐለ አላመሩም።

እርስበርስ ግንኙነት

በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሽረ ላይ ያለ ጎል አቻ ሲለያዩ ጅማ ላይ ጅማ 2-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ወንድወሰን አሸናፊ

ዓወት ገብረሚካኤል – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ሀብታሙ ሽዋለም – ነፃነት ገብረመድህን

ዲዲዬ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ሳሊፍ ፎፋና

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

መሐመድ ሙንታሪ

ጀሚል ያቆብ – መላኩ ወልዴ – ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገብረሥላሴ – ኤፍሬም ጌታቸው

ሱራፌል ዐወል – ኤልያስ አሕመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ

ያኩቡ መሐመድ


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ