የአዳማ ከተማ እንቆቅልሽ አልተፈታም

በሜዳም ከሜዳም ውጭ በተደራራቢ ችግር ውስጥ የሚገኘው እና መፍትሔ ሊያገኝ ያልቻለው የአዳማ ከተማ ጉዳይ መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሏል።

ባልተቋጨ ችግር በአሰልጣኙ አሸማጋይነት ባሳለፍነው ሳምንት ለጨዋታው ሰዓታት ሲቀረው ወደ ድሬደዋ በመጓዝ 2-1 በሆነ ውጤት በመሸነፍ የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ከድሬደዋ መልስ በኃላ ቃል ተገብቶላቸው የደሞዝ ክፍያ ባለመፈፀሙ ምክንያት ዳግም ችግሩ አገርሽቶ ያለፉትን አምስት ቀናት አስገራሚ ጊዜዎችን እያሳለፈ ይገኛል።

ከዛሬ ነገ የደሞዝ ክፍያው ይፈፃማል በማለት በአመራሮቹ ላይ ጫና ለማሳደር ለወትሮ መደበኛ ልምምድ የሚሰሩበት አበበ ቢቂላ ስታድየምን በመተው በግላቸው ልምምድ እየሰሩ ይገኛል። እስካሁን ባለው የአምስት ቀናት የልምምድ መርሐግብራቸው ከቡድኑ የአሰልጣኞች አባላት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እያደረጉ አለመሆናቸው አግራሞትን ሲጭር ይህ ማለት ተጫዋቾቹ አሰልጣኝ አልባ ልምምድ እየሰሩ ይገኛሉ ማለት ነው።

የክለቡ የበላይ ጠባቂ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ተጫዋቾቹን ባልተፈቱ ችግሮች ዙርያ በመነጋገር መፍትሔ ይገኝበታል ተብሎ የታሰበው ቀጠሮ ሳይሳካ መቅረቱ ተጫዋቾቹ ተሰፋ ጥለው የነበረበት ጉዳይ ሳይሳካ ቀርቷል።

ተጫዋቾቹ ቀሪ ደሞዛችን ካልተከፈለን አንጫወትም በሚለው አቋማቸው ፀንተዋል። ቀጣይ ከእሁድ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የሚኖረውን የሊጉ ጨዋታ የመጫወቱ ጉዳይም አለየለትም። በቀጣይ ክለቡ ለተጫዋቾቹ የደሞዝ ክፍያውን ይፈፅማል ወይስ አሰልጣኙ በድጋሚ ከመደበኛ ስራቸው በመውጣት የአሸማጋይነት ተግባራቸው ይሰማራሉ የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኖ ይቀጥላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ