አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስለ ቀጣይ የማጣርያ ጨዋታዎች ይናገራሉ

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በቅርቡ ሽግሽጎች በተደረጉበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድልን አስመልክቶ በፌደሬሽኑ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመጪው የፈረንጆቹ ሴፕቴምበር ይካሄዳል ተብሎ አስቀድሞ መርሐግብር ተይዞለት የነበረውን የኒጀሩ የደርሶ መልስ ጨዋታ ወደ መጋቢት መጠጋቱን አስመልክቶ ተካታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“አስቀድሞ ወጥቶ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ መርሃግብር በመቀየሩ የተነሳ የእቅድ ለውጥ ለማድረግ ተገደናል፤ በዚህም አስቀድመን ይዘነው ከነበረው የረጅም ጊዜ እቅድ ወጥተን ካለን የሁለት ወር ጊዜ ጋር ተስማሚ የሆነ የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥተናል። አስቀድመን በያዝነው እቅዳችን መሠረት የመጪው የፈረንጆች ማርች ወር ላይ በሚኖረው የፊፋ መስኮት ተጠቅመን የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግ ሥራዎችን እየሰራን እንገኝ ነበር። በተለይም ከኮትዲቫር ጨዋታ ድል መልስ ከተለያዩ የሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥያቄዎች ቀርበውልን ነበር። በተለይ ከካሜሮን አቻችን ጋር ጨዋታ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ነበር።

“አሁን በተቀየረው መርሐግብር መሰረት ከኒጀር ጋር በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በአንድ ሳምንት ልዩነት የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን እናደርጋለን። በዚህ ምክንያት አስቀድመው ያዘጋጀነው አቅድ ሙሉ ለሙሉ ተፋልሷል። በዚህም ወደ አማራጭ እቅድ ለመግባት ተገደናል። ሁለተኛው እቅዳችን የሆነው በአሁኑ ወቅት ሊጉን እየመራ ከሚገኘው የሊጉ ዓብይ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ውድድሮችን በማይነካ መልኩ የተመረጡ ተጫዋቾችን በሳምንት ለሁለት ያክል ቀናት የምናገኝበትን መንገድ ለመፍጠር ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል። በእኛ በኩል እንደ እቅድ የያዝነው ማክሰኞና ረቡዕን ለመጠቀም አቅደናል። በዚህም መሠረት በሁለቱ ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ አራት መርሐ ግብሮችን ለመከወን ታቅዷል። ይህም ማክሰኞ ጠዋት ላይ የክፍል ውስጥ የንድፈ ሀሳብ ቆይታ የሚኖር ሲሆን ከማክሰኞ ከሰዓት ጀምሮ እሮብ ጠዋትና ከሰአት ላይ የሜዳ ላይ የተግባር ልምምዶች ለመስራት እቅዶችን አዘጋጅተናል።

“በማክሰኞው የክፍል ውስጥ ክፍለ ጊዜ ላይ ከእግርኳስ ውጭ የሥነ ምግብ፣ ሥነ ልቦና እና ታክቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎች ለማድረግ ታቅዷል። ተጫዋቾች ውድድር ላይ ስለሆኑ የአካል ብቃት ስራዎች ላይ ብዙም ሥራዎች አይጠበቅብንም። አዲሱ እቅዳችን ተበትኖ የነበረውን ብሔራዊ ቡድናችን ተጫዋቾች ወቅታዊ ብቃትን በተከታታይ ለመለካት ይረዳናል ብለን እናስባለን።

“ሌላው በአዲሱ እቅዳችን መሠረት ከኒጀር የደርሶ መልስ ጨዋታ በፊት አንድ በሜዳችንና አንድ ሌላ ጨዋታ ደግሞ ከሜዳ ውጭ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እኔ በግሌ እንዲሁም የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት በሥራ አጋጣሚ ከሚያገኟቸው ሰዎች በከሉ ለማሳካት እየሰራን እንገኛለን።”

ስለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ

” ውድድሩ ከስያሜው አንፃር ለማለፍ የሚደረግ ማጣሪያ እንደመሆነለ እንደሁሉም ቡድኖች እኛም ለማለፍ እንሰራለን ፤ ምድቡን የሚመጥን ጠንካራ ስራ እንድንሰራ ከእኛ ይጠበቃል። በምድባችን የሚገኙት ደቡብ አፍሪካና ጋና ካላቸው የካበተ ልምድ አንፃር ቀላል እንደማይሆን እንገምታለን።

“በተያያዘም በቀጣይ ለምናደርጋቸው ማጣሪያዎች ግብዓት ለመሰብሰብ ይረዳን ዘንድ በእግር ኳሱ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን ጋብዘን ሀሳብ ለመሰብሰብ ታቅዷል፤ በተመሳሳይ ከፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ጋር በመሆን ከመገናኛ ብዙሃን አባላት ጋር በቀጣይ ብሔራዊ ቡድን ግንባታ ዙርያ ምክክር ለማድረግም እቅድ ይዘናል።”

በመቀጠል አሰልጣኞች በስፍራው ከታደሙ የሚድያ አካላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተው መርሐግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ