የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ

በፕሬዝዳንቱ እና በሥራ አስፈፃሚዎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ዛሬ ሊካሄድ የነበረው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።

በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል። ሆኖም ምልዓተ ጉባዔው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኃላ በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት የመክፈቻ ንግግር ተደርጎ ም/ፕሬዝደንቱ አቶ በለጠ ዘውዴ የ2011 ሪፖርትም ሆነ የ2012 ዕቅድ እኛ የማናውቀው በፕሬዝዳንቱ ብቻ የቀረበ በመሆኑ አንቀበለውም በማለታቸው እንዲሁም አቶ ነጋሲ (የሥራ አስፈፃሚ አባል) ፌዴሬሽኑ የቡድን ሥራ አይሰራም፣ ህግ አይከበርም፣ ግለሰባዊ ነገሮች ይበዛሉ ይህ የሚቀርበው ሪፖርትም አናቀውም በማለታቸው በተጨማሪም የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈለቀ ዋቄ የኦዲት ሪፖርቱ ማስታወቂያ ወጥቶ ውድድር ይደረግ ሲባል ከፅህፈት ቤቱ እውቅና ውጭ የተካሄደ በመሆኑ እና ሪፖርቱ እና እቅዱም በተመሳሳይ ከእውቅና ውጭ መፈፀም የለበትም በማለት ለጉባዔው አቅርበዋል።

ፕሬዝደንቱ ኃይለየሱስ ፍስኃ በበኩላቸው ሁሉም ነገር የተካሄደው ህጉን ደንቡን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት በ2011 ሪፖርት እና በ2012 ዕቅድ ዙርያ ሀሳብ ይስጥ በማለት መድረኩን ክፍት አድርገዋል።

ከዚህ በኃላ የነበሩት የጉባኤው መንፈሶች እጅግ መግባባት የጎደለው በሥራ አስፈፃሚዎቹ በኩል የሰፋ ልዩነት የነበረበት እና መተማመን ያልሰፈነበት ሆኖ ቀጥሎ በመጨረሻም አሉ የተባሉ ችግሮችን አጣርተው ለቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ የሚያቀርቡ አምስት አጣሪ ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ በመምረጥ ጉባዔው ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።

የአጣሪ ኮሚቴ አባላት

አቶ ዳንኤል ኃ/ሚካኤል
አቶ ዐቢይ ካሣሁን
አቶ ገዛኸኝ ታደሰ
አቶ ሰለሞን
አቶ ታምሩ

ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን እንመልሰበታለን


© ሶከር ኢትዮጵያ