ሪፖርት | ሰበታ በሜዳው ነጥብ መሰብሰቡን ቀጥሎበታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሰበታ ከተማ ሀዋሳን 2-1 በመርታት ለጊዜውም ቢሆን ደረጃውን ያሻሻለበትን ሙሉ ሦስት ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።

ባለሜዳዎቹ በመቐለ ከተሸነፈው የቡድን ስብስብ ውስጥ የአንድ ተጫዋቾች ለውጥ ብቻ ሲያደርጉ በዚህም በጌቱ ኃይለማርያም ምትክ በባለፈው ጨዋታ ግብ ማስቆጠር የቻለው እንዳለ ዘውገ በቀዳሚ ተመራጭነት ጀምሯል። በአንፃሩ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ወልቂጤን ከረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም አዲስዓለም ተስፋዬ፣ አለልኝ አዘነ እና መስፍን ታፈሰን በዛሬው ጨዋታ ወደ መጀመርያ 11 የተመለሱ ተጫዋቾች ሆነዋል።

በቅርቡ ከወላይታ ድቻ አሰልጣኝነት የለቀቁት አሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራ በስታዲየም ተገኝተው በተከታተሉት በዚሁ ጨዋታ ከጨዋታው መጀመር በፊት የሀዋሳው የመሐል ተከላካይ ላውረንስ ላርቴን ከካሶተኒው ስር የለበሰው ነጭ ካልሲ እንዲያወልቅ በዳኛው በመታዘዙ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ዘግይቶ ለመጀመር ተገዷል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ወደራሳቸው ሜዳ ሰብሰብ ብለው ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች መስፍን ታፈሰ ወደ ተሰለፈበት የግራ መስመር ባነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ሀዋሳዎች ወደ ጎል በመድረስ ከባለሜዳዎቹ የተሻሉ ነበሩ። በአንፃሩ ሰበታዎች በኳስ ቁጥጥር እንዲሁም አልፎ አልፎ በሚጣሉ ቀጥተኛ ኳሶች ያፈገፈገውን ሀዋሳ ተጫዋቾች አልፈው ወደ ጎል ለመድረስ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ አልነበሩም።

ጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስተናገድ 17 ያክል ደቂቃ ፈጅቶበታል። በዚህም የሰበታ ተጫዋቾችን ቅብብል ተስፋዬ መላኩ አቋርጦ ያቀበለውን ብሩክ በየነ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ከግቡ አናት በላይ የመጣችበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበረች።

በተመሳሳይ በ26ኛው ደቂቃ ተስፋዬ መላኩ ከራሳቸው ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ መስፍን ታፈሰ በጥረቱ ከተከላካዮች አፈትልኮ በማምለጥ በግራ እግሩ የሞከረውን ኳስ ዳንኤል አጄ አድኖበታል። ሀዋሳዎች ከዚህ ሙከራ ጋር በሚመሳሰሉ ሒደቶች በተደጋጋሚ በግራ መስመር ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም በመስፍን ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ሲባክኑ ተስተውሏል።

ሰበታዎች በአንፃሩ በ31ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከተከላካዮች አልፎ የሞከረውን ቤሊንጋ ባዳነበት ሙከራ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረታቸውን የጀመሩ ሲሆን በ35ኛው ደቂቃ ከእጅ ውርወራ የተነሳው ኳስ የላውረንስ ላርቴ ስህተትን ተጠቅሞ ከጠበበ አንግል ባኑ ዲያዋራ አክርሮ የመታውን የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ቤሊንጋ ሲመልስ ፍፁም ገ/ማርያም ከቅርብ ርቀት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሀዋሳዎች የጨዋታውን ውጤት ለመቀልበስ ያለመ ቅያሬ አድርገዋል። በዚህም የመስመር ተከላካዩ አዲስዓለም ተስፋዬን አስወጥተው አጥቂው ሄኖክ አየለን በማስገባት ሁለተኛውን አጋማሽ በሦስት አጥቂዎች ለመጫወት ሞክረዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ እንደ ቡድን የማጥቃት ፍላጎታቸው ጨምሮ በታየበት በዚሁ አጋማሽ በጣም የተሻለ ቡድን ሆነው ቀርበዋል። እንደመጀመሪያው ሁሉ በዚህም አጋማሽ የአለልኝ አዘነ የኳስ ስርጭትና የተመጠኑ ረጃጅም ኳስ ስኬት የሚያስደንቅ ነበር።

ሁለቱ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች መስፍን እና ብሩክን በመጠቀም አደጋ ለመፍጠር ጥረት ያደርጉ የነበሩት ሀዋሳዎች በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ያላቸው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ተግዳሮት ሆኖቧቸው ተስተውሏል። በተጨማሪም በሁለኛው አጋማሽ በርካታ ተጫዋቾች በማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ማረጋቸው በተለይ የመልሶ ማጥቃት ተጋላጭነታቸውን ጨምሮት ተስተውሏል። ለማሳያነት በ60ኛው ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ እንዲሁም 68ኛው እና 87ኛው ደቂቃ ፍርዳወቅ ሲሳይ ያገኟቸው አደገኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በ73ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም ካመከናት አስቆጭ አጋጣሚ በማስከተል በሀዋሳው ግብጠባቂ ቤሊንጋ ኢኖህ ስህተት በተገኘ እድል ከመስመር የተሻረለትን ኳስ ተጠቅሞ አዲስ ተስፋዬ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ያሳደገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በደቂቃዎች ልዩነት በሰበታ ከተማዎች በኩል ተቀይሮ የገባው ፍርዳወቅ ሲሳይ በተመሳሳይ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን እጅግ አስደናቂ ኳስ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ሶስተኛውን ግብ ማስቆጠር በቻሉ ነበር።

በ79ኛው ደቂቃ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከአይቮሪኮስት ጋር በነበረው ጨዋታ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ርቆ የሰነበተው የሰበታው የመሀል ተከላካይ አንተነህ ተስፋዬ ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ወደ ሜዳ ተቀይሮ በመግባት ለአዲሱ ቡድኑ የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታ ማድረግ ችሏል።

የሀዋሳ ከተማዎች ተደጋጋሚ የማጥቃት ጥረት በስተመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ በ81ኛው ደቂቃ በጨዋታው ብኩን ሆኖ የዋለው መስፍን ታፈሰ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ በባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብ ለሀዋሳ ማስቆጠር ችሏል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ወጣቱ አጥቂ መስፍን ታፈሰ ባጋጠመው ጉዳት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ረዘም ላለ ደቂቃ ሜዳ ላይ ህክምና እርዳታ ሲደረግሉት ቆይቶ ራሱን በመሳቱ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ለማምራት ተገዷል።

በቀሩት ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ጨዋታው በሰበታ ከተማዎች የ2-1 የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ