የአሰልጣኞች አስተያየት| ሰበታ ከተማ 2-1 ሀዋሳ ከተማ

በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ሀዋሳን 2ለ1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

👉 “ሜዳው ለመጫወት በጣም ከባድ ነበር” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ስለጨዋታው

“ማሸነፋችን ደስ አስኝቶኛል ፤ ከሽንፈት መምጣታችን በራሱ ይዞት የሚመጣው ጫና አለ። ከዛ ለመውጣት ያሳየነው ነገር ጥሩ ነው ብዬ ነው የማምነው። ከዚህ ውጭ ሀዋሳ ከተማ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ያሉት ቡድን ነው። በተጨማሪም የተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ያሉት ቡድን ነው። ከዚህ ቡድን ጋር በምትፈልገው መልኩ ለመጫውት ሞክረህ ማሸነፍ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በዛሬው ጨዋታ ላይ በተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ላይ እንደነበሩት አይነት ጥቃቅን ስህተቶች ነበሩብን፤ እነዚህን በቀጣይ እያረምን እንሄዳለን። እንደ አጠቃላይ ወደ አሸናፊነት መመለሳችን በሥነልቦና ረገድ ለእኛ ጥሩ መነቃቃት ይፈጥርልናል።”

የቡድኑ ተጫዋቾች ላይ ስላሉ መሻሻሎች

“በእርግጠኝነት ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ አግኝተናል ለማለት አይቻልም። አራት አምስት የሚሆኑ በጉዳት ሜዳ ላይ የሌሉ ተጫዋቾች አሉ። በተለያዩ ተጫዋቾች እየተጠቀምን መጫወት የምንፈልግበት መንገድ በሂደት እየገባቸው መጥቷል ብሎ መናገር ይቻላል። በአንድ ጊዜ ሀሳቡ ቢገባቸውም ሜዳ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ግን ከባድ ነው። ሜዳው ዛሬ እንዳያችሁት ለመጫወት በጣም ከባድ ነበር በዚህ ሜዳ ላይ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እጅግ ከባድ ነው። ወደ ግብ ጠባቂ የሚመለሱ ኳሶች እጅግ አስፈሪ ነበሩ፤ ኳሶቹ ፈረስን እንደመያዝ በጣም የከበዱ ነበሩ። ፌደሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስብበት ይገባል። የምንጫወትበት ሰዓት በራሱ 9 ሰአት መሆኑ ከባድ ነው። በተጨማሪ ደግሞ የመጫወቻ ሜዳው ምቹ አለመሆኑ ነገሮችን ከባድ ያደርጋቸዋል። ኳስ ለሚያውቅ ሰው በዚህ ሜዳ ላይ ስለኳስ ማውራት በጣም ከባድ ነው። እንደው ቢቻል ከጨዋታ በፊት ሜዳው ውሃ ሊጠጣበት የሚችለው መንገድ ቢመቻች ቢያንስ የምንፈልገውን ሀሳብ ለመተግበር እንሞክራለን። በተጨማሪም 10 ሰው እንኳን ቢሆን ወደ ሜዳ የሚገባው ሰው በጨዋታው ለመዝናናት እስከመጣ ድረስ መሠረታዊ ነገሮች አንዱ በሆነው በተሻለ የመጫወቻ ሜዳ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ መመልከት ይገባዋል።”

👉 “በመከላከሉም በማጥቃቱም ረገድ መረጋጋት ተስኖን ነበር” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“በመከላከሉም በማጥቃቱም ረገድ መረጋጋት ተስኖን ነበር። የገቡትም ጎሎች መረጋጋት ባለመቻላችን የተቆጠሩ ናቸው። ኳስ ጨዋታን የምታሸንፈው በጎል ስለሆነ የተሻለ ስላገቡ አሸንፈውናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበረው መሻሻል

“አንዳንድ ጊዜ ጎል ስታስተናግድ ይበልጥ አጥቅተህ ለመጫወት ትሞክራለህ። በመጀመሪያው አጋማሽ ከሜዳ ውጭ ያደረግነው ጨዋታ እንደመሆኑ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገናል። ቢሆንም ሁለቱም ግቦች ከበረኛ የተመለሱ ኳሶች ነው የተቆጠሩት። ይህ የትኩረትና ያለመረጋጋት ችግሮች እንደነበሩ ያሳያል። በተጨማሪም ከእነሱ በተሻለ ነፃ የግብ አጋጣሚዎችን አግኝተን መጠቀም አልቻልንም። ወደ ጨዋታው ስንገባ ለማሸነፍ ነበር የመጣነው ግን ጎል ማስቆጠር ባለመቻላችን ተሸንፈናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ