መስፍን ታፈሰ በድጋሚ ጉዳት አስተናግዷል

ለሳምንታት በጉዳት ከሜዳ በመራቅ ዛሬ ሀዋሳ ከተማ ከሰበታ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ የተመለሰው መስፍን ታፈሰ ዳግመኛ ጉዳት አስተናግዷል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ሰበታ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 2-1 በረታበት ጨዋታ ላይ የሀዋሳን የማስተዛዘኛ ብቸኛ ጎል በማስቆጠር እና በግሉ መልካም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተመለከትነው ወጣቱ አጥቂ መስፍን ታፈሰ ከአንተነህ ተስፋዬ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት ጉዳት አስተናግዷል።

ያጋጠመው ጉዳት ጉንጩ አካባቢ የመድማት እና የማበጥ ሲሆን ከዚህ ውጭ በውስጥ አካሉ ላይ የማይታይ ሌላ ጉዳት ሊኖር ይችላል በሚል ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተሻለ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ በቀጥታ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ሊያመራ ችሏል።

ከክለቡ የህክምና ባለሙያ አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት ህክምናውን ተከታትሎ የጉዳቱ መጠን የተሰጋውን ያህል አስጊ ባለመሆኑ እና በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኝ ስለሆነ ቡድኑ ወዳረፈበት ሀራምቤ ሆቴል ማምራቱን ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ