ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

መደረጉ አጠራጣሪ የነበረው የአዳማ ከተማ እና የሃዲያ ሆሳዕና ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በሜዳም ሆነ ከሜዳም ውጪ ባሉ ችግሮቹ ተተብትቦ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማ ኅዳር 27 የተቀዳጀውን ብቸኛ ድል (ወልቂጤ ከተማን 1-0) በአዕምሮ በማሰላሰል የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃል።

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ አቻ አቻ

 

ከደሞዝ ጋር በተያያዘ መደበኛ ልምምዳቸውን ከአሰልጣኞች ቡድን ጋር እየሰሩ የማይገኙት የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች ለቀናት በተናጥል (ግማሾቹ በሰፈር በሚገኝ ሜዳ ተሰባስበው) ልምምዶችን ሲሰሩ ነበር። እርግጥ የተጨዋቾቹ የደሞዝ ጥያቄ ቀደም ባሉት ቀናት ሲሰነዘር ቢሰማም ዛሬ ከሰዓት የከተማው ከንቲባ አቶ አህመድ የቡድኑን ተጨዋቾች በመሰብሰብ ጥያቄያቸው በአፋጣኝ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚፈቱ ገልፀውላቸው የነገውን ጨዋታ እንዲያደርጉ እንዳስሟሟቸው ተሰምቷል።

ከሜዳ ውጪ ያሉ ችግሮች የበረቱበት ቡድኑ የሜዳም ላይ እንቅስቃሴውም የተሻለ አይደለም። አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈ ቡድን የሆነው ክለቡ ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር ተጠናውቶታል። እርግጥ በእንቅስቃሴ ደረጃ ከተለያዩ አማራጮች ግቦችን ለማስቆጠር ቢታትርም ፍሬያማ የመሆን ችግር ይታይበታል። ምናልባት ይህ ጉዳዩ በነገው ጨዋታ የማይደገም ከሆነ ጥሩ ነገሮችን ሊፈጥር ይችላል።

ረጅሞቹ እና ፈርጣማዎቹ የቡድኑ ተከላካዮች የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን የተከላካይ ክፍል አጠናክሮታል። ተጨዋቾቹ በመከላከል ብቻ ሳይሆን የማጥቃት ኳሶችን በማስጀመር እና የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ቡድናቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት መንገድ ተደናቂ ነው። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ምናልባት ከቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶች ግቦችን ለማስቆጠር ከፈለገ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾቹ ጥረት ዋጋ ሊከፍከው ይችላል።

አዳማ ከተማዎች አማኑኤል ጎበናን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ አዲስ ህንፃ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ሚካኤል ጆርጅ አሁንም ጉዳት ላይ በመሆናቸው ከስብስባቸው ውጪ አድርገዋል።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ

በ6ኛ ሳምንት የደረሰባቸው የ5-0 ሽንፈት (በኢትዮጵያ ቡና) ያነቃቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ካገኙት ጥሩ የውጤት ጎዳና ላለመውጣት እና ከአንድ ጨዋታ በፊት ያስመዘገቡትን የሜዳ ውጪ ድል ለመድገም ወደ አዳማ አምርተዋል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ቡድኑ ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ መንገድ እየገባ ይመስላል። በተለይ ሁለቱ ቢስማኮች (አፒያ እና ኦፖንግ) የቡድኑን የፊት መስመር ጨዋታ በጨዋታ እያሻሻሉ መጥተዋል። ከእነዚህ ተጨዋቾች በተጨማሪ በመስመሮች መካከል በመገኘት አደጋዎችን ለመፍጠር የሚታትረው አብዱልሰመድ ዓሊ በነገው ጨዋታ ለአዳማ ከተማ ተከላካዮች ፈተና እንደሚሆን ይገመታል።

ከዚህ ውጪ ይሁን እንደሻው እና አፈወርቅ ኃይሉ የሚልኳቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ለቡድኑ ወሳኝ ናቸው። እርግጥ አዳማ ካለው የአየር ላይ ጥንካሬ አንፃር ቡድኑ በተሻጋሪ ኳሶች ሊጠቀም እንደማይችል ቢገመትም ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን ተጠቅመው ሆሳዕናዎች ግብ ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ይገመታል።

በተጋባዦቹ በኩል ምንም የጉዳትም የቅጣትም ዜና የለም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለሁለት ጊዜያት ተገናኝተው ሁለቱንም አዳማ ከተማ አሸንፏል። አዳማ 4 ጎሎች ሲያስቆጥር ሆሳዕና አንድ አስቆጥሯል።

– በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ በ2008 የተገናኙት በ10ኛው ሳምንት አዳማ ላይ ሲሆን ከአራት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሲገናኙም ቦታው አዳማ፤ ሳምንቱም አስረኛ ሆኗል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (3-4-3)

ደረጄ ዓለሙ

ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – መናፍ ዓወል

በላይ ዓባይነህ – ኢስማኤል ሳንጋሪ – ከነዓን ማርክነህ – ሱሌይማን መሐመድ

በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ – ቡልቻ ሹራ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

አቤር ኦቮኖ

ፀጋሰው ዴልሞ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቃታ

ፍራኦል መንግስቱ – አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው – አብዱልሰመድ ዓሊ – ሄኖክ አርፊጮ

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ


© ሶከር ኢትዮጵያ