ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ

በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የባህር ዳር ከተማን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

የማይገመት ጉዞ እያደረጉ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው ሳምንት ነጥብ ከጣሉበት የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ መልስ ዳግም የአሸናፊነትን መንገድ ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ

በሊጉ ከፍተኛ የአቻ ውጤቶች (5) ያስመዘገበው ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞ ጥንካሬዎቹ እየከዱት የመጡ ይመስላል። በተለይ ጨዋታዎችን በሚገባ ተቆጣጥሮ ማሸነፍ እየቻለ የማይገኘው ቡድኑ በተከታታይ 2 የሜዳ ላይ ድሎቹን በመድገም ወደ አሸናፊነት ለመምጣት የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይለዋል። ነገር ግን ቡድኑ በጉዳት ምክንያት ወጥ የሆነ የአጥቂ መስመር ጥምረት ለመገንባት በመቸገሩ በነገው ጨዋታ ግብ አካባቢ እንዳይቸገር አስግቷል። በቀኝ መስመር የሚሰለፈው እና ከሰሞኑን ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው ጋዲሳ መብራቴ ጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

የፈረሰኞቹ የተከላካይ መስመር በተለይ መሀል ለመሀል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት መጠነኛ ክፍተቶች ሲያስመለክት ተስተውሏል። በዚህ መነሻነት የባህር ዳር የአማካይ ተጨዋቾች የሚፈጥሯቸው ጥቃቶች ቡድኑን ሊረብሽ እንደሚችል ከወዲሁ እንዲገመት አድርጎታል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሳልሃዲን ሰዒድ፣ አቤል እንዳለ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ለዓለም ብርሃኑ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ

ከሜዳው ውጪ የሚደረጉ ጨዋታዎችን የማሸነፍ አይናፋርነት ያለበት ባህር ዳር ከተማ የሜዳ ላይ ድሎቹን በማጣጣም ጉዞውን ቀጥሏል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ የዓመቱን የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድል ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ለመቀዳጀት አዲስ አበባ ገብቷል።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ አሰልጣኝነት የሚመራው ቡድኑ ግቦችን የማስቆጠር ችግር የለበትም። ከምንም በላይ ከተለያዩ አጨዋወቶች ግቦችብ የሚያመርተው ቡድኑ ለተጋጣሚ የሚያሳየው አይገመቴነት ሲጠቅመው ተስተውሏል። በተለይ ከወገብ በላይ ያሉት የቡድኑ ተጨዋቾች የሚያደርጉት ጥረት ቡድኑን በየጨዋታው ተጠቃሚ አድርጎታል። ነገር ግን በተደጋጋሚ በሁለተኛ አጋማሽ እየተዳከመ የሚመጣው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ላይ ጉልበቱን አመጣጥኖ ካልተጫወተ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እራሱን ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል።

በቡድኑ ውስጥ ነፃ ሚና የሚሰጠው ፍፁም ዓለሙ መስመር ላይ ከሚሰለፉት አጥቂዎች ጋር(ምናልባት ግርማ እና ዜናው) የሚያደርገው መስተጋብር ባለሜዳዎቹን ለከረብሽ ይችላል። ከዚህ ውጪ አዳማ ሲሶኮ እና ማማዱ ሲዲቤን የያዘው ቡድኑ በቆሙ ኳሶች ግቦችን ለማስቆጠር እንደሚጥር ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

ባህር ዳር ከተማዎች በነገው ጨዋታ የወሰኑ ዓሊን እና የአቤል ውዱን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱንም ጨዋታዎች ባህር ዳር በተመሳሳይ ውጤት 1-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ደስታ ደሙ – አስቻለው ታመነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ምንተስኖት አዳነ – የአብስራ ተስፋዬ

ጋዲሳ መብራቴ – ጌታነህ ከበደ – አቡበከር ሳኒ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪስተን ሄሱ

ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – ሰለሞን ወዴሳ – ሚኪያስ ግርማ

ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፍፁም ዓለሙ

ግርማ ዲሳሳ – ማማዱ ሲዲቤ – ዜናው ፈረደ


© ሶከር ኢትዮጵያ