ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሲዳማ ቡና

የ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2ኛ ቀን መርሐ ግብሮች መካከል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የፋሲል ከነማ እና የሲዳማ ቡናን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በሜዳቸው እጅግ ጠንካራ ከሆኑ ክለቦች መካከል ቀደሚ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ያገኙትን ጣፋጭ የሜዳቸው ላይ ድሎች ለመድገም እና ባሳለፈነው ሳምንት ወደ መቐለ አምርተው በስሑል ሽረ ከተሸነፉበት ጨዋታ ስሜት ለመውጣት 9 ሰዓትን ይጠብቃሉ።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ አቻ

 

በእንቅስቃሴ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በውጤት ደረጃም ጥሩ ጉዞ በሜዳቸው እያደረጉ ያሉት ፋሲል ከነማዎች የነገው ጨዋታ እንደሌሎቹ የሜዳቸው ላይ ግጥሚያዎች ቀላል እንደማይሆንላቸው ይገመታል። እርግጥ ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና ከሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ወገብ በታች (9ኛ) ቢቀመጥም በእንቅስቃሴ ደረጃ የሚያሳየው ጥንካሬ ፋሲልን እንደሚፈትን እንዲገመት አድርጎታል። ነገር ግን ቡድኑ በተለይ በአይደክሜዎቹ ሽመክት እና ሱራፌል ብቃት እና ታታሪነት ታግዞ ነጥብ ከሜዳው ይዞ ለመውጣት እንደሚጥር ይታሰባል።

በሊጉ ላይ እየተሳተፉ ካሉ 16 ክለቦች ብዙ ጎሎችን ተጋጣሚ ላይ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ(17) ነገም ከእየአቅጣጫው ግቦችን ለማግኘት እንደሚታትር ይገመታል። ለዚህም ለብዙ የጨዋታ ስልቶች አመጪ የሆኑ ተጨዋቾች ቡድኑ በመያዙ ሲዳማዎች የተከላካይ ክፍላቸው ስራ በዝቶበት እንደሚውል ይታሰባል። ቡድኑ ስል የሆነ የፊት መስመር ቢኖረውም በቀላል ስህተቶች ግብ የሚያስተናግድበት መንገድ በነገው ጨዋታ ችግር ውስጥ እንዳይከተው አስግቷል። በተለይ ፈጣኖቹ የሲዳማ የፊት መስመር ተጨዋቾች በመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን እንዳይሰነዝሩበት ያሰጋል። በዚህም በአማካይ ስፍራ ላይ የሲዳማን መልሶ ማጥቃት የመመከት አላማ ያለው የተጫዋቾች ምርጫ እንደሚኖራቸው ይገመታል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በነገው ጨዋታ እንየው ካሳሁን እና ያሬድ ባዬን በጉዳት እንደማያሰለፉ ተገልጿል።

(በኤዲት የተካተተ፡ ሀብታሙ ተከስተ እና ጋብሬል አህመድ በጉዳት ለዚህ ጨዋታ እንደማይደርስ ተነግሯል።)

የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

 

በሊጉ ላይ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል እስካሁን ምንም ጨዋታ አቻ ያልወጣው እና ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የተሸነፈው ሲዳማ ቡና እያደረገ ያለውን ወጣ ገባ አቋም ለማስተካከል በማለም የዓምና የዋንጫ ተፎካካሪውን ቡድን ነገ ይገጥማል።
በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚሰለጥነው ቡድኑ ከተጋጣሚው ፋሲል ከነማ ቀጥሎ በሊጉ ብዙ ጎሎችን ተጋጣሚ ላይ ካስቆጠሩ 2 ክለቦች (ሌላኛው ባህር ዳር ከተማ ነው) መካለል አንዱ ነው። በተለይ የቡድኑን 68.75 % (11 ጎል) ግብ ያስቆጠሩት አዲስ ግዳይ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ ፍጥነታቸውን ተጠቅመው የሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ተጋጣሚን ሲረብሽ ይታያል። በነገውም ጨዋታ እነኚህ 3 ተጨዋቾች አልፎ አልፎ የትኩረት ማነስ ችግር ላለበት የፋሲል ከነማ የተከላካይ ክፍል ፈተና እንደሚሆኑ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ የፋሲል ተጨዋቾች ለማጥቃት ትተውት የሚወጡትን ቦታ በፍጥነት በመጠቀም በጎ ነገሮችን ለቡድናቸው ለማምጣት እንደሚጥሩ ይታሰባል።

9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ከስሩ ካሉ 7 ክለቦች 3ኛው ብዙ ግቦችን የሚያስተናግድ ክለብ ነው(ድሬዳዋ 18፣ ሃዲያ 16 ሲዳማ 14)። ይህ ግብ የማስተናገድ ችግሩ በየጨዋታው ግብ ለሚጠማው የፋሲል የፊት መስመር በጎ ነገሮችን ይዞ እንዳይመጣ አስግቷል። በተለይ ከመስመር የሚነሱ እና ሙጂብን በመሬት እና በአየር ላይ ያነጣጠሩ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ቡድኑ በአግባቡ ካልመከተ 3 ነጥብ አስረክቦ ሊወጣ ይችላል።

በቡድኑ በኩል ሚሊዮን ሰለሞን አሁንም ከጉዳት ባለማገገሙ ወደ ጎንደር እንዳላመራ ታውቋል።

9 ሰዓት የሚጀምረውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ አማራጮቹ ለስፖርት ቤተሰቡ በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሊጉ እስካሁን 6 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና አራት በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ፋሲል ከነማ አሸንፏል። ሲዳማ 10 ሲያስቆጥር ፋሲል 6 ማስቆጠር ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚካኤል ሳማኬ

ዓለምብርሀን ይግዛው – ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ሱራፌል ዳኛቸው -መጣባቸው ሙሉ – በዛብህ መለዮ

ኦሲ ማውሊ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሃ – ሰንደይ ሙቱኩ – ግርማ በቀለ – ተስፉ ኤልያስ

ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሐንስ –

አዲስ ግደይ – ዳዊት ተፈራ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ይገዙ ቦጋለ


© ሶከር ኢትዮጵያ