“የነገውን ጨዋታ ይበልጥ ተጠናክረን ለማሸነፍ ነው የምንገባው” የዩጋንዳ U-17 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አዩብ ካሊፋ

ህንድ ለምታስተናግደው የዓለም የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመካፈል የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታቸውን ለማከናወን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዩጋንዳዎች በሶሊያና ሆቴል በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ነገው ጨዋታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በቅድሚያ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አዩብ ካሊፋ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። “ኢትዮጵያ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ። ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤታችን ናት። ለነገው ጨዋታ በደንብ ተዘጋጅተናል። በሜዳችን 2-0 ብናሸንፍም የተወሰኑ ፈተናዎች ገጥመውን ነበር። በነገው ጨዋታ ግን እነዛን ፈተናዎች ተመርኩዘን ስራዎችን ስለሰራን ለጨዋታው ዝግጁ ነን። በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ የመጣነው ለማሸነፍ ነው። ስለዚህ የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ ዝግጁ ነን።”

በመቀጠል የቡድኑ አምበል ጁሌት በአጭሩ የሚከተለውን ብላለች።” እኔን ጨምሮ ሁሉም ተጨዋቾች ለነገው ጨዋታ ተዘጋጅተናል። በነገው ጨዋታ ዋነኛ ግባችን ማሸነፍ ነው። ኢትዮጵያ ጥሩ ሃገር ነች። የአየር ንብረቱን ጨምሮ ብዙ ነገሮች ጥሩ ናቸው። እንዳልኩት ግን የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው።”

ከአምበሏ ሀሳብ በኋላ የተወሰኑ ጥያቄዎች ተሰንዝረው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አዩብ ካሊፋ ምላሽ ሰጥተዋል።

ስለ መጀመሪያው ጨዋታ?

እንደጠቀስኩት ጨዋታውን ብናሸንፍም የተወሰኑ ፈተናዎች ገጥመውን ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀላል ቡድን አይደለም። እርግጥ በመጀመሪያው አጋማሽ የትኩረት ማነስ ችግር ታይቶባቸው ነበር። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ይህንን ችግራቸውን ቀርፈው ለመቅረብ ሞክረው ተጫውተዋል። እኛም ከነሱ በኩል የገጠመንን ፈተና ለማስተካከል በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተናል።

ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን?

ጠቅለል አድርጎ ስለ ቡድኑ ለማውራት ጥሩ ተጨዋቾች አሏችሁ። በመጀመሪያውም ጨዋታ ይህንን በደንብ ተመልክቻለሁ። ነገር ግን የእኔ ተጨዋቾች ጠንካራ ናቸው። የሚገጥማቸውን ፈተናዎች በአግባቡ የሚጋፈጡ ተጨዋቾች በመያዜ ደስተኛ ነኝ።

ስለ ነገው ጨዋታ እቅዳቸው?

ዋነኛው እና የመጀመሪያው እቅዳችን ጨዋታውን ማሸነፍ የሚል ነው። በሜዳችን 2-0 ብናሸንፍም አንዘናጋም። እንደውም የነገውን ጨዋታ ይበልጥ ተጠናክረን ለማሸነፍ ነው የምንገባው።

ትላንት አመሻሽ ወደ ባህር ዳር የገቡት እና ማረፊያቸውን በዊን ሆቴል ያደረጉት ዩጋንዳዎች ዛሬ ከ10:30-11:14 የቆየ ቀላል ልምምድ አከናውነዋልል። በልምምድ መርሐ ግብሩም ቡድኑ ሳቅን የሚፈጥሩ የማፍታቻ እና ቀላል የማፍታቻ ስራዎችን ሲሰራ ታይቷል። 

ጨዋታውን የሚመሩት አሊን ዩሙቶኒ (ዋና)፣ ኒይኒዋአባሪ (የመጀመሪያ ረዳት)፣ ሙካይራንጋ (ሁለተኛ ረዳት) እና ሙካንሳንካ (አራተኛ) ከሩዋንዳ ወደ ባህር ዳር ገብተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ