የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 መቐለ 70 እንደርታ

ወላይታ ድቻ በአስረኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቐለ 70 እንደርታን በሜዳው አስተናግዶ 1-0 ከረታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተውናል፡፡
👉 “ድሉ የማሸነፍ ፍላጎታችን ያመጣው ውጤት ነው” ደለለኝ ደቻሳ (የወላይታ ድቻ ጊዜያዊ አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው

” እንዳያችሁት ነው፡፡ ከገብረክርስቶስ ቢራራ ስንብት በኋላ በተጫዋቾቹ አዕምሮ ላይ በደንብ ስንሰራ ነበር። ለመጫወት ያለንም ፍላጎት ጥሩ ነው፡፡ ድሉ ፍላጎታችን ያመጣው ውጤት ነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደነበረን ብልጫ ያለመጠቀም ነገር ታይቷል፡፡ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቶሎ ቶሎ ወደፊት በመላክ ነበር ስንጫወት የነበረው። በሁለተኛው አጋማሽ የአጨዋወት መንገዳቸውን ለውጠው ከፊት ሰው በመቀነስ አምስት አድርገውብን ነበር፡፡ ስለዚህ ኳሱን የግድ ስበን መጫወት ነበረብን። በቁጥር ከኋላ ብዛት ስላላቸው እኛም ከኃላ ያለውን ነገር ቀርፈን ቀስ እያልን ወደፊት ለማጥቃት ነበር የፈለግነው። እነሱ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዞ ለመሄድ ነበር አላማቸው። በዚህ ሒደት የተቀዛቀዘ ይመስላል።

በሁለተኛው አጋማሽ ያገኘነውን ለመጠቀም ነበር ያሰብነው። ሆኖም ግን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ገልበን ብንጫወት በመልሶ ማጥቃት ሊያገቡብን ስለሚችሉ ጥንቃቄን ለመምረጥ ተገደናል፡፡

👉 “ሜዳው በሚፈቅደው መልኩ ባለመጫወታችን ጥሩ እንዳንንቀሳቀስ አድርጎናል” ገብረመድህን ኃይሌ (መቐለ 70 እንደርታ )

ሜዳው በሚፈቅደው መልኩ ባለመጫወታችን ጥሩ እንዳንጫወት አድርጎናል። እዚህ እንደሜዳው መጫወት ያስፈልጋል፤ እሱን በልምምዳችን በዚሁ ሜዳ ላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ መረጋጋትን አልመረጥንም እንጂ አንድ ቡድን ቀድሞ ካገባ አሸናፊ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ቢሆንም ግን በአጠቃላይ ሰላማዊ ነው ደስ ይላል፡፡ መሸናነፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህ ሽንፈታችን ወጥተን ደግሞ ያለውን ሁኔታ ለማስቀጠል ጥረት እናደርጋለን፡፡

የአማኑኤል ገብረሚካኤል አለመኖር

“አማኑኤል የሚጠቅመን ተጫዋች ነው። የሱ ያለመኖር በዕርግጥ ጎድቶናል። እሱ ቢኖር ተጋጣሚ ላይ ከስሙ አንፃር የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖረው ነበር፡፡ በማጥቃቱ ጥሩ አልነበርንም። በአጠቃላይ ከመሐል የሚመጡ ኳሶች ከባዶች ስለነበሩ አሸንፈው ለመውጣት ችለዋል፡፡ በአጠቃላይ አጋጣሚን መጠቀም ነው እዚህ ሜዳ ላይ የሚያስፈልገው፡፡ አማኑኤል ግን በቀጣይ ይደርስልናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ