ሪፖርት | የቸርነት ጉግሳ ብቸኛ ግብ ለወላይታ ድቻ ተከታታይ ድል አስገኝታለች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኙ ስንብት በኋላ በሜዳው መቐለን በመርታት ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡

ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ሳምንት የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታቸው ከሜዳቸው ውጪ ጅማን ከረታው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አንድም ተጫዋቾች ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ በሜዳቸው ሰበታን አሸንፈው የመጡት መቐለ 70እንደርታዎች በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርገዋል፡፡ በተጎዳው አማኑኤል ገብረሚካኤል ምትክ ኤፍሬም አሻሞን፣ በጋናዊው ተከላካይ ላውረንስ ኢድዋርድ ምትክ አሚኑ ነስሩን ቀዳሚ ተመራጭ አድርገው ገብተዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ጨዋታውን በሚገባ በመቆጣጠር መርተው በፈፀሙት ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድን ሲከተሉ የነበረ ቢሆንም ወላይታ ድቻዎች ከተሻጋሪ እና በቅብብሎሽ ወደ መቐለ ግብ ክልል በመድረሱ ረገድ ግን የተሻሉ ነበሩ፡፡ በተለይ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር በአማካይ ስፍራ የተሰለፈው እድሪስ ሰዒድ በሁለቱ መስመሮች ላይ ለተሰለፉት ቸርነት ጉግሳ እና እዮብ ዓለማየሁ ቶሎ ቶሎ ሲያሻግራቸው የነበሩት አስፈሪ ኳሶች ለመቐለ የተከላካይ ክፍል ከብደው የታዩ ከመሆኑም በዘለለ ወላይታ ድቻዎች ብልጫ ለመውሰዳቸው ማሳያም ነበር።

መቐለ 70እንደርታ በጨዋታው ላይ የጎል ሙከራ በማድረግ ረገድ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን ከዚህች ሙከራ ውጪ ግን ወደ ድቻ ሳጥን ለመጠጋት ተቸግረዋል። 9ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ወደ ጦና ንቦቹ የግብ ክልል የመጡት ምዓም አናብስቱ ኦኪኪ አፎላቢ አክርሮ መቶ ተከላካዩ ውብሸት ዓለማየሁ ቀድሞ ደርሶ በግንባሩ ለግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ አቀብላለው ሲል ኳሷ አቅጣጫዋን ስታ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታለች፡፡

ከፈጣሪ አማካዩ እድሪስ እግር ስር በሚነሱ አደገኛ ኳሶች በቀኝ እና ግራ በኩል በተሰለፉት ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ድቻዎች እንደ ነበራቸው ብልጫ ግን ያደረጉት የግብ ሙከራ ጥቂት ነው፡፡ 18ኛው ደቂቃ እድሪስ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ ያሻገራትን ቸርነት አግኝቷት ወደ ሳጥን የመቐለን ተከላካይ አልፎ ከፊሊፕ ኦቮኖ ጋር ተገናኝቶ ኳሷን ቢመታትም ኳሷ አቅጣጫዋን ስታ ወጥታለች። አሁንም በቸርነት ጉግሳ ተጠግተው መጫወትን ምርጫ ያደረጉት አረንጓዴ ለባሾቹ 43ኛው ደቂቃ እድሪስ አሁንም ምርጥ ኳስ ለባዬ ሰጥቶት ባዬ ላይ ኦቮኖ ሲደርስበት ኦቮኖንም ኳሷ አልፋ እዮብ ከግቡ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መረጋጋት ባለመቻሉ ወደ ላይ ሰዷታል፡፡

ከእረፍት መልስ እንግዳው ቡድን መቐለ ኤፍሬም አሻሞን በአሸናፊ ሀፍቱ ለውጠው ካስገቡ በኃላ ማጥቃት ላይ በተወሰነ መልኩ ለመነቃቃት የሞከሩ ሲሆን ድቻዎች በበኩላቸው ከመጀመሪያው አጋማሽ አጨዋወታቸውን ተቀያሪ ተጫዋቾችን በማስገባት ረጃጅም ኳስ ላይ ያተኮረን መልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ታትረዋል፡፡

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽም ቀዳሚ ሙከራን ያደረጉት ሞዓብ አናብስቶች ነበሩ፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት በሰራው የመዘናጋት ስህተት ያሬድ ከበደ አግኝቷት ለሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ሰጥቶት አማካዩ ወደ ግብ ቢመታውም መክብብ ደገፉ በቀላሉ ይዞበታል፡፡ መቐለዎች በአኪኪ አንድ ጊዜ ብቻ ሙከራ ማድረግ ከቻሉ በኃላ ከእንቅስቃሴ ውጪ የግብ አጋጣሚም ሲፈጥሩ አላስተዋልንም፡፡

75ኛው ደቂቃ ላይ ባለሜዳዎቹ ተሳክቶላቸው የማሸነፊያ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ ከማዕዘን ምት እድሪስ ሰዒድ ሲያሻማ የመቐለ ተከላካዮች ጉልህ ስህተት ታክሎበት ያሬድ ዳዊት ወደ ግብ መትቶት ፊሊፕ ኦቮኖ መመለስ ቢችልም ግቡ አጠገብ የነበረውና ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ባለፈው ሳምንት መመለስ የቻለው ቸርነት ጉግሳ ሳይቸገር ወደ ግብነት ቀይሯት ድቻዎችን መሪ አድርጓቸዋል፡፡

በቀሩት ሀያ አምስት ደቂቃዎች ከእንቅስቃሴ እና ወላይታ ድቻዎች አስጠብቆ ለመውጣት ከሚያደርጉት ሰዓት የማባከን ስትራቴጂ ውጪ ተጨማሪ ግልፅ የሆኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳንመለከት ጨዋታው በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

❖ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወላይታ ድቻ እና ረጅም ኪሎ ሜትር አቋርጠው የመጡት የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች በስታዲየሙ ውስጥ የጋራ ዝማሬን ያደረጉበት እና የተመሰጋገኑበት መንገድ አስገራሚ እና ለሊጉ ቡድኖች ትምህርት የሰጠ ሆኖ አልፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ