“ከኔ የተሻለ ነገር ጠብቁ” ጎድዊን ቺካ 

 

የኢትዮጵያ ተወካዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲሸልሱ ሴንት ሚሸልን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ በዚህ ጨዋታ ክለቡን በጥር የዝውውር መስኮት የተቀላቀለው ናይጄሪያዊው ጎድዊን ቺካ ለፈረሰኞቹ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጎ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ የአጥቂ አማካይ እና አጥቂ ሆኖ መሰለፍ የሚችለው ቺካ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት በ80ኛው ደቂቃ ኳስን ከመረብ አዋህዷል፡፡

ተጫዋቹ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን ግብ ማስቆጠሩ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡ “በመጀመሪያ ጨዋታዬ ግብ ማስቆጠር በመቻሌ በጣም ተደስቻለው፡፡ አሰልጣኜ አምኖብኝ ስላጫወተኝ አመሰግናለው፡፡ ለቡድኑ ኃላፊ ኤፍሬምም ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው፡፡ እሱም ልክ እንደአሰልጣኜ በኔ ላይ ትልቅ ዕምነት ነበረው፡፡”

ቺካ እንደሚናገረው ከሆነ ግብ ማስቆጠር ጥሩ ጎኑ እንደሆነ እና ግቦችን ለፈረሰኞቹ ማስቆጠር እንደሚቀጥል ይገልፃል፡፡ “የመጀመሪያ ጨዋታዬን እንዳማድረጌ እና ግብ ማስቆጠር መቻሌ ለኔ ጥሩ የሞራል መነሳሳት ይፈጥርልኛል፡፡ ከዚህ በኃላም ግብ ማስቆጠር እንደምችል ዕምነቱ አለኝ ምክንያቱም ጥሩ ጎኔ የግብ ማስቆጠር ብቃቴ ስለሆነ፡፡ ስለዚህም ከኔ የተሻለ ነገር ጠብቁ፡፡” በማለት ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡

ያጋሩ