ከጨዋታ በፊት ቀይ ካርድ – እንግዳ ክስተት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቆ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሯል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞም እንግዳ ክስተት ተፈጥሯል።

ተጫዋቾች አሟሙቀው ለጨዋታ ወደ ሜዳ በሚመለሱበት ወቅት የባህር ዳር ከተማው ግብጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ የለበሰው መለያ ቁምጣ ቀለም ከቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ቀለም ጋር ስለሚጋጭ እንዲቀይር በዳኛው ቴዎድሮስ ምትኩ ቢታዘዝም እሰጣ ገባ ውስጥ በመግባቱና ያልተገባ ባህርይ አሳይቷል በሚል ቀጥታ ቀይ ካርድ ሊመለከት ችሏል።

ይህን ተከትሎም በሕጉ መሠረት ተጫዋቹ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በቀይ ካርድ በመወገዱ በምትኩ ተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድ ጨዋታውን ጀምሯል። ሀሪስተንም በተመልካች መቀመጫ ሆኖ ጨዋታውን እየተከታተለ ይገኛል።

ሀሪስተን ሄሱ በኢትዮጵያ ቆይታው ይህ ሁለተኛ ቀይ ካርዱ ሆኖ ተመዝጎቧል።

©ሶከር ኢትዮጵያ