በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ባህርዳር ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀይደር ሸረፋ በ58ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት አስደናቂ ግብ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ አብዱልከሪም መሐመድ፣ አቤል ያለው እና ሙሉዓለም መስፍን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አካተው ሲጀምሩ ባህር ዳር ከተማዎች ወልዋሎን ከረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ተከላካዮቹ ሄኖክ አቻምየለህ፣ ሳሙኤል ተስፋዬና አማካዩ ሳምሶን ጥላሁን ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት ገብተው የዛሬውን ጨዋታ ማድረግ ችሏል። በዛሬው ጨዋታ ወደ ተጠባባቂ ወንበር የወረደው አዳማ ሲሶኮ ምንም እንኳን በተጠባባቂነት ጨዋታውን ቢጀምርም እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ከመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊዎች ጋር ልምምዱን ይሰራበት የነበረበት የትጋት መጠን ትኩረት የሚስብ ነበር።
ሌላው ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ለመግባት ሲጠባበቁ ጨዋታውን በመጀመሪያ ተመራጭነት ጀምሮ የነበረው የባህር ዳሩ ግብጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ ከእለቱ ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በፈጠረው አለመግባባት ቀጥታ ቀይ ካርድ በመመልከቱ በጽዮን መርዕድ ተተክቷል። ሁኔታውን ተከትሎ በተፈጠረው ንትርክ ጨዋታው ለ15 ያክል ደቂቃዎች ዘግይቶ ለመጀመርም ተገዷል።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመስመሮች በኩል በተለይ በቀኝ መስመር ተሰላፊያቸው ጋዲሳ መብራቴ በኩል ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ የታየበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነበር።
የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው ገና በ3ኛው ደቂቃ ነበር። የባህር ዳር ከተማው የመስመር አጥቂ ዜናው ፈረደ ከመስመር አጥብቦ የገባውና ከሳጥን ጠርዝ ተጫዋቾች አልፎ ወደ ግብ የላካት ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ሊያድበት ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች አፀፋ ለመስጠት የፈጀባቸው የሰከንዶች ጊዜ ነበር። በ4ኛው ደቂቃ ከጉዳት መልስ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የተመለሰው አብዱልከሪም መሐመድ የግርማ ዲሳሳ ትኩረት ማነስን ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ከባህር ዳር ሳጥን ቀኝ ጠርዝ በቀጥታ ወደ ተቃራኒ የግብ ቋሚ አክርሮ መትቶ ጽዮን መርዕድ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ የጨዋታውን ጅማሮ ትኩረት ሳቢ ያደረጉ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ያለ ግብ በተጠናቀቀው በዚሁ አጋማሽ የባህር ዳር ከተማዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ አስፈሪ ነበር። በተለይም ከግዙፉ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ጀርባ በነፃነት የመጫወት ፍቃድ የተሰጠው ፍፁም ዓለሙ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማስጀመርና እንቅስቃሴውን በማስቀጠል ረገድ እንደወትሮው ሁሉ መድመቅ ችሏል። በዚህም እንቅስቃሴ ባህርዳሮች በ12ኛው ፍፁም ያስጀመረውን ኳስ ሲዲቤ ከግራ መስመር አጥብቦ ገብቶ የሞከረውና ማታሲ ያዳነበት እንዲሁም በ15ኛው ደቂቃ ፍፁም በተመሳሳይ ያስጀመረውንና በግራ መስመር ለተሰለፈው ግርማ አቀብሎት በተመሳሳይ ማታሲ ያዳነበት፤ በተጨማሪም በ30ኛው ማማዱ ሲዲቤ አቀብሎት ፍፁም ያመከናት ኳስ ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት ምን ያህል አስፈሪ መሆኑን ያስመሰከሩ ሙከራዎች ነበሩ።
በሒደት ወደ ጨዋታው እየገቡ የመጡት ፈረሰኞቹ በ15ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ወደ ግብ የላከውና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት አጋጣሚ ጨምሮ በ39ኛውና በ45ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች ጀርባ በተጣሉ ኳሶች ጌታነህ ከበደና አቤል ያለው ከፅሆን መርዕድ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝተው የመከኑት ኳሶች ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ስለነበራቸው አንፃራዊ የበላይነት ምስክር ናቸው።
በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ከሳምንታት በኋላ በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ተሰልፊነት የተጫወተው የጊዮርጊሱ የመስመር ተከላካይ አብዱልከሪም መሐመድን በደስታ ደሙ ቀይረው ያስገቡት ፈረሰኞቹ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በባህርዳር ከተማ የበላይነት ተወስዶባቸው ነበር።
በእነዚህም ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ነበር። በተለይም በ50ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ዜናው ፈረደ ከማታሲ ጋር ተገናኝቶ ማታሲ ያዳነበት እንዲሁም በ53ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሳምሶን ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ፍፁም ሞክሮ ማታሲ ሲያድንበት በቅርብ ርቀት የነበረው ዜናው ፈረደ ከሳጥን ጠርዝ ሞክሮ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣበት ኳስ ተጠቃሾች ናቸው።
ፈረሰኞቹ በ57ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋጥረዋል። ምንተስኖት አዳነ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ያሻማውን ባህር ዳር ሳጥን ጠርዝ ላይ የነበረው ሀይደር ሸረፋ ኳሷ እንደመጣች በመጀመሪያ ንኪኪ ግሩም ግብን አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በፊት ኳሷን አመቻችቶ ያቀበለው ምንተስኖት አዳነን በአሜ መሐመድ ለመተካት ተዘጋጅተው የነበሩት የፈረሰኞቹ አለቃ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ ከቡድኑ ተጫዋቾች በተለይ ከጌታነህ ከበደ በደረሰባቸው ተቃውሞ ቅያሬውን ለማዘግየት ተገደው የነበረ ቢሆንም ቅያሬው ለ10 ያክል ደቂቃዎች ዘግይቶ ተተግብሯል።
ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ በቡድኑ ውጤት ደስተኛ ያልሆኑት የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች በአሰልጣኙ ላይ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ ተስተውሏል
በተቀሩት ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ግብን ይፈልጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዞ ለጥንቃቄ ቅድሚያ ሰጥተው ተመልክተናል።
በ80ኛው ደቂቃ ላይ በዛሬው ጨዋታ አሳዳጊ ክለቡን በተቃራኒ እየገጠመ የነበረው ወጣቱ የባህር ዳር ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ ሳሙኤል ተስፋዬ በአቤል ያለው ላይ በፈፀው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ባህር ዳር ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ ብቸኛ የፊት አጥቂያቸው ማማዱ ሲዴቤን በጥልቀት ወደ ኃላ ስበው ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎች ኢላማ ያደረጉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊሶች 1-0 የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ