አንድ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ ወደ ሆስፒታል አመራ

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደ የሊጉ 10ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በፀጥታ አካላት በደረሰበት ጉዳት አንድ ደጋፊ ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

በዕለቱ ጨዋታውን በሚመሩት ዳኛ ውሳኔ አሰጣጥ ክፉኛ ሲበሳጩ የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በዕለቱ ዳኛ ላይ ተቋውሞ እያሰሙ ባለበት ወቅት አንድ የፀጥታ አካል በአንድ የሆሳዕና ደጋፊ ላይ በወሰደው ከልክ ያለፈ ድብደባ ምክንያት ራሱን በመሳቱ በቀይ መስቀል አንቡላስ በፍጥነት ወደ ኃይለማርያም ሆስፒታል አምርቷል።

ደጋፊው በደረሰበት ጉዳት ራሱን ስቶ መውደቁን የተመለከቱ ሌሎች የሆሳዕና ደጋፊዎች ህይወቱ ያለፈ መስሏቸው በድንጋጤ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጣቸውን ወደ ፀጥታ አካላት ድንጋይ በመወርወር ገልፀዋል። ሜዳ ላይ የነበሩ የሆሳዕና ተጫዋቾችም ብስጭታቸውን በመግለፅ ከፀጥታ አካላት ጋር ፀጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል።

ጉዳት የደረሰበት ደጋፊ ነቅቶ ጉሉኮስ ተደርጎለት በአሁኑ ሰዓት በኃይለማርያም ሆስፒታል አልጋ ቁጥር 21 በመተኛት ህክምናውን እየተከታተለ ይገኛል።

10ኛ ሳምንት በደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምንም እንኳ የጎላ የፀጥታ ችግር ባይፈጠርም ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም የፀጥታ አካላት በቀላሉ መቆጣጠር የሚችሉትን ችግር ከልክ ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰዳቸው ምክንያት ችግሩ ሊባባስ ችሏል። በቀጣይም እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይደገሙ አወዳዳሪው አካል ክትትል ሊያደርግ ይገባል።


© ሶከር ኢትዮጵያ