መከላከያ በሜዳው እጅ የሰጠባቸው ታክቲካዊ ድክመቶች

 

መከላከያ በአፍሪካ የኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ በግብፁ ምስር አል ማቃሳ በሜዳው 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ የአምናው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ በሜዳው የተቆጠሩበት ጎሎች መብዛት የመልሱን ጨዋታ ይበልጥ ከባድ ያድርጉበታል፡፡

በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚ ላይ እምብዛም የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ያልቻለው መከላከያ በደካማ የቡድን አደረጃጀት እና በተናጥል የተጫዋቾቹ የወረደ አቋም በሜዳው ማግኘት የሚገባውን ውጤት አሳጥቶታል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ማጥቃት ላይ ያመዘኑት እና የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት በመጠነኛ ጥናት የቃኙት ማቃሳዎች በ4-4-2/4-4-1-1 ፎርሜሽን ሲጠቀሙ ቢታዩም በአብዛኛው ማለት ቢቻል መልኩ የመከላከል መስመራቸው ላይ 5 ተጫዋቾችን በጎንዩሽ ሲደረደሩ ተስተውለዋል፡፡ የገብረመድህን ኃይሌው ቡድን ደግሞ ያለተፈጥሮዊ የመስመር አጥቂዎች እና ለሲስተሙ አመቺ ባልነበሩት የመሃል አማካዮች 4-3-3ን ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡

ምስል 1

1

መከላከያ ያልተጠቀመበት በመስመሮች የነበረ ሰፊ ክፍተት

የሁለቱም ቡድኖች የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ወደ መካከለኛው የሜዳ ክልል የተጠጋ አቋቋምና እንቅስቃሴ ነበራቸው፡፡ የምስር አል ማቃሳ የመስመር ተከላካዮች ጨዋታው እንደተጀመረ በተለይ በቀኝ በኩል ሆስኒ አህመድ መጠነኛ የፊት ለፊት የማጥቃት ሩጫዎችን በመስመሩ ላይ ሲከወኑ ነበር፡፡

የግብፁ ቡድን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጎሎችን በማስቆጠርና በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ደግሞ በመከላከል ላይ በማተኮር በጨዋታው ሂደት እና በሜዳው ከፍታ (altitude) ከሚመጣው ከፍተኛ ድካም ወይም መዛል (fatigue) ለመዳን በሚመስል በተለመደ የሰሜን አፍሪካ እና ሌሎች ዝቅተኛ ከፍታ ካላቸው (lower altitude) ሃገራት የሚመጡ ቡድኖች እንደሚያደርጉት አይነት ስትራቴጂ ነበረው፡፡ በዚህኛው እቅዳቸው መሰረት በቀኝ መስመር ላይ በፈጠሩት መጠነኛ ጫና በመከላከያው የግራ መስመር ተከላካይ ታፈሰ ሰርካ ከጎል ክልሉ ቀኝ ጠርዝ አካባቢ በተፈጠረ ስህተት የተገኘውን ቅጣት ምት የመከላከል ግድግዳ ለመስራት ከቆሙት ሁለት የመከላከያ ተከላካዮች አናት በላይ “ቺፕ” ተደርጋ ያለፈችን ኳስ ተጠቅሞ አብድል ሞሀስን የመጀመሪያውን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

የአሰልጣኝ ኤልሃብ ጋኤል ቡድን ወደ መሃለኛው የሜዳ ክፍል ተጠግቶ የመከላከል (highline defending) እና የጠበበ የአማካይ ክፍል (narrow midfield) ቅርፅ ነበረው፡፡ ይህም ቅርፅ በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ለድክመት ሊያጋጣቸው የሚችለውን በተጫዋቾች መሀከል የሚኖረውን የጎንዬሽ እና የፊት ለፊት ክፍተትን ለማጥበብና በማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የጎል ክልል ለመድረስ ሰፊ ርቀት እንዳይሸፍኑ አግዟቸዋል፡፡

ማቃሳ አጥብቦ ሲጫወት የመከላከያም ቅርፅ እንዲሁ መጥበቡ (norrow መሆኑ) ለመከላከያ የመጀመሪያው አጋማሽ ያልተሳካ የጨዋታ አቀራረብ አይነተኛ ምክንያት ነበር፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ላይ በአዲሱ እና በሽመልስ ተገኝ መካከል የነበረው ክፍተት (channels) በመጠቀም አምር ባራካት 2ኛ ጎል አስቆጥሮ መሪነታቸውን ያጠናከረላቸው በመከላከያ የጎንዮሽ ጥበት (lateral narrowness) ምክንያት ነበር፡፡

እንዲህ የጠበበ ቅርፅ ማጥቃትን አስቀድሞ ኋላ ላይ መከላከልን ኢላማ ላደረገውና ከመዛል የሚመጣ የአቋም መውረድን ለመከላከል ያለመው አል ማቃሳን የሜዳውን የጎንዬሽ ክፍተት በማስፋት የተጠቀጠቀውን የተጫዋቾች አቋቋም መበታተን ፤ ተቀራርቦ የሚጫወተው የተከላካይ ክፍል ላይ ጫና ማሳደር እንዲሁም የመከላከያ አጥቂዎችና አማካዮች ተቀራርበው ወደ ፊት በመጓዝና ጥልቀት (depth) በመፍጠር በማቃሳ ተጫዋቾች መካከል ያለውን መጠቅጠቅ (horizontal compactness) በመቀነስ እና ክፍተትን በመፍጠር ማቃሳ የተሻለ እንዳይንቀሳቀስ ማገድ ይቻል ነበር፡፡

ምስል 2

2

የአማካይ ክፍል

የመከላከያ የአማካይ ክፍል በአንድ የተከላካይ አማካይ እና በግራ እና ቀኙ በሚሰለፉ ተጫዋቾች (Midfield shutters) የተዋቀረ ነው፡፡ Midfield shuttlers በሁለት ተጫዋቾች ለተደራጀው እና ለተከላካይ አማካዩ በጎንዬሽ ቅርብ ርቀት ላይ ለሚገኙ በሜዳው ቁመት ለሚመላለሱ ሁለቱ አማካዮች የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ስያሜው በጠባብ diamond midfield ለሚጫወቱት ሁለቱ አማካዮችም ያገለግላል፡፡

ሚናው ከተጫዋቾች አካላዊ ፍጥነት ፤ ቴክኒካዊ ክህሎት ፤ የጨዋታ ሂደትን በፍጥነት የመረዳት አዕምሮአዊ ብቃት እንዲሁም ጥልቀት ያለው የተጋጣሚን ቡድን እንቅስቃሴ አረዳድ ይሻል፡፡ በጨዋታው የማጥቃትና የመከላከል ሂደቶ ላይ የተመረኮዘ በሜዳው ቁመት የሚደረግ ተደጋጋሚ የመመላለስ (shuttling) እንቅስቃሴ ስለሚፈለግም ከፍተኛ አካል ብቃትን ይጠይቃል፡፡

ከመስመር ተከላካዮች ጋር በመናበብ በማጥቃት እንቅስቃሴ የመቀባበያ አማራጮችን መጨመር ፣ ከመስመር አጥቂዎች ጋር በመናበብ በተጋጣሚ በላይኛው የሜዳ ክፍል የማጥቃት ማዕዘናትን ማስፋት ፣ በመከላከል ወቅት ደግሞ ከመስመር ተከላካዩ እና የመስመር አጥቂው ጋር በመሆን በተጋጣሚ ላይ የቁጥር ብልጫን ማስገኘት መሰረታዊ እና ተጠቃሽ የተጫዋቾቹ ሃላፊነቶች ናቸው፡፡  በላይኛው የሜዳ ክፍል በመገኘትም ጎሎችን ማስቆጠርና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ሁሉ ለማድረግ ደግሞ እንቅስቃሴያቸው እጅግ የተጠና አንዲሆን ያስፈልጋል፡፡

በጨዋታው ከበኃይሉ ግራ እና ቀኝ የተሰለፉት ፍሬው እና ሚካኤል ጥቂቱን እንኳ በአግባቡ ሲከወኑ አልተመለከተንም፡፡ የበኃይሉ እጅግ ወደ ኃላ ያፈገፈገ የቦታ አጠባበቅ ከሚካኤልና ከፍሬው እንዲርቅ አድርጎታል፡፡ ይህም ሚካኤል እና ፍሬውን ከበሃይሉ ፊት ለፊት በሰፊ ርቀት እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ የአደራደር ቅርፁም ወደ 4-1-2-3 እንዲለውጥ አስገድዷል፡፡ በዚህም ምክንያት ሚካኤልና ፍሬው በሜዳው ቁመት በጎንዬሽ ሊኖራቸው የሚገባውን ቦታ አጠባበቅ እንዳይተገብሩ አስገድዷቿል፡፡ ይህ ሲፈጠር የመስመር አጥቂዎች እና የመስመር ተከላካዮቹ በተፈጠረው ሰፊ የመስመሮች ክፍተት እየተገኙ ክፍተቱን (ቦታውን) መሸፈን ቢገባቸውም ያን ሲያድርጉ ብዙም አልታዩም፡፡ ይህም መከላከያን በመስመሮች የመናበብ እና የመተጋገዝ ውህደትን (lines coherence) እንዲያጣ አስገድዶታል፡፡ በመሰመር አጥቂነት የተሰለፉት ምንይሉና ባዬ እጅግ ወደ መሃል የተጠጋ ሩጫቸውና ቦታ አያያዛቸው ፋይዳ አልባ የነበረውም ለዚህ ይመስላል፡፡

3

ከእረፍት መልስ

ከእረፍት መልስ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ በ1-1 ግንኙነት ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ በአግዳሚው ላይ የሰደዳትኳስ በፊት መስመር ተጫዋቾቻችን ላይ ያለውን ደካማ የአጨራረስ ብቃት አመላካች ነበር፡፡ መከላከያዎች ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ መሀመድ ናስርን በማስገባት ወደ 3-4-3 የተለወጠ ፎርሜሽን ተጠቅመዋል፡፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር እጅግ ከጠበበ ማዕዘን ኤል ሳይድ ሄዊ ለቡድኑ 3ኛ አስቆጥሮ ለመከላከያ ጨዋታውን አክብዶበታል፡፡ በ89ኛው ደቂቃ መሀመድ ናስር በጥሩ ቴክኒካዊ ብቃት ለመከላከያ ግብ ቢያስቆጥርም ከማስተዛዘኛነት አላለፈችም፡፡

የመጨረሻው የማቃሳ ጎል መከላከያ አማካይ በመጨመር እና ተከላካይ በመቀነስ ሲጫወት የሚዛናዊነት (balance) ችግር እንደሚያሳይ አመላካች ነበር፡፡ በአገራችን እግር ኳስ ያልተለመዱና ያልተሰራባቸው ጥቂት ለውጦች ወዲያው አሉታዊ ጎናቸው ፍንትው ብሎ የመታየቱ ምክንያትም የቅርፅም ይሁን የተጫዋቾች የሚና ቅያሬዎች መሰረታዊና ተደጋጋሚ ልምምድ ስለሚያንሳቸው ነው፡፡

ያጋሩ