ምንተስኖት አሎ ቱርክ ገብቷል

የሙከራ ዕድል አግኝቶ ወደ ውጭ እንደሚሄድ የተነገረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብጠባቂ ምንተስኖት አሎ በሠላም ቱርክ ገብቷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ ሁኔታ አንድ ግብጠባቂ የውጭ ዕድል አግኝቶ ወደ አውሮፓ ባልተጓዘበት እግርኳሳችን ምንተስኖት አሎ በቱርክ ዋናው ሊግ በሚወዳደረው አንታልያስፖር እና በሁለተኛው የሊግ እርከን በሚገኘው ደሚርስፖር በተባሉ ሁለት ክለቦች የሙከራ ዕድሉን እግኝቶ ሊጓዝ እንደሆነ መዘገባችን ይታወቃል።

ትናንት ማምሻውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን በረራውን ያደረገው ምንተስኖት እኩለ ሌሊት ላይ ቱርክ ኢስታንቡል መግባቱን በሀገር ውስጥ ሆኖ ጉዳዩን በመከታተል ዕድሉ እንዲመቻች ያደረገው እንዳለኢየሱስ አባተ (የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወንድም እና የቀድሞ የአአ ከተማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ) አሳውቆናል።

ግብዣውን ባቀረቡለት ወኪል አማካኝነት ቱርክ አየር ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል እንዳደረጉለት እና በቱርክ በሚኖረው ቆይታ በተለያዩ ክለቦች የሙከራ ዕድሉን በቅርብ እንደሚጀምር ሰምተናል።


የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብጠባቂ የሆነው ምንተስኖት አሎ በቱርክ በሚኖረው ቆይታ መልካም ዕድል እንዲገጥመው ሶከር ኢትዮጵያ እየተመኘች በቱርክ የሞኖረውን እንቅስቃሴ እየተከታተልን ዘገባዎችን የምናቀርብ መሆናችንን ከወዲሁ እንጠቁማለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ