በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም 10ኛ ሳምንት ጨዋታውን ያድረገው አዳማ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከሰባት ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ድል አስመዝግቧል።
ወደ ድሬ አቅንተው በሽንፈት ከተመለሰው ስብስባቸው ያልተጠቀሙባቸውን ግብጠባቂው ጃኮ ፔንዜ፤ ሱሌይማን ሰሚድ፣ አዲስ ህንፃ እና አማኑኤል ጎበናን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመመለስ ሲጠቀሙ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሜዳቸው አንድ አቻ ከተለያየው ስብስባቸው ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ስድስት የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ በመዘዙበት እና ከሆሳዕና ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ተቃውሞ እያስተናገዱ በመሩት ጨዋታ አዳማ ከተማዎች እንዳለባቸው ውስብስብ ችግሮች የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ በቻሉበት የመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል።
12ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ለቀኝ መስመር ያደላ ቅጣት ምት ያገኙት አዳማ ከተማዎች ዳዋ ሆቴሳ በሚገርም ሁኔታ የሆሳዕናው ግብ ጠባቂ አቤር ኦቮኖ አቁሞት ቀዳሚውን ጎል አስቆጥሯል። አዳማዎች ከጎሉ መቆጠር በፊት በኅብረት አጨዋወት ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ጎል ካስቆጠሩ በኃላ የበለጠ ተነቃቅተው ይጫወታሉ ቢባልም በእንቅስቃሴ ወርደው ተመልክተናል።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት እንግዶቹ ሀዲያዎች በእንቅስቃሴ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ጎል በአፈወርቅ እና በይሁን አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ኢላማውን ያልጠበቀ በመሆኑ እና ለግብጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ሲሳይ ሆነው መክነዋል። ይሁን እንጂ 22ኛው ደቂቃ ቢስማርክ አፒያ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር አምስት ከሀምሳ ውስጥ የሚገኘው ፍራኦል መንግስቱ አቀብሎት ኳሱን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ባልተለመደው ቀኝ እግሩ መቶት ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ ምን አልባት በሚጫወትበት ግራ እግሩ ኳሱን ቢጠቀምምበት ኖሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ የሚችል የጎል ዕድል ነበር።
በዚህ የሆሳዕና የማጥቃት ሒደት ውስጥ በአዳማ በኩል በረከት ደስታ ከቅጣት ምት ያሻገረው ዳዋ ሆቴሳ ወደ ጎል ደገፍ አድርጎ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።
የዕለቱ ዳኛ በሚወስኗቸው ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት የሆሳዕና ተጫዋቾች ተቃውሞ ማሰማት የጀመሩት አዳማዎች ያገኙትን የመልስ መት ከግብጠባቂው ጃኮ ተቀብሎ ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ ኳስ አርቃለው ብሎ በስህተት ለሆሳዕና አጥቂ ቢስማርክ ኦፖንግ ደርሳ ራሱን ቴዎድሮስን ለማለፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ቢስማርክ ኦፖንግ ላይ ጥፋት ተሰርቶ ዳኛው በዝምታ አልፈዋል በሚል ነበር።
የጨዋታው እንቅስቃሴ በተለያዩ ውዝግቦች እየተቆራረጠ ባለበት ሂደት ውስጥ ፈገግ የሚያሰኝ ድርጊት እና ጨዋታውን ለሁለት ደቂቃ እንዲቋረጥ ያደረገ ክስተት ሜዳ ውስጥ ተከስቷል። ከስታድየሙ ካታንጋ አቅጣጫ ሳይታሰብ የስታድየሙን አጥር በማለፍ የመጣ ውሻ ሜዳው ውስጥ በመግባቷ ከሜዳው ለማስወጣት የተደረገው ጥረት ፈገግ ያሰኝ ነበር።
ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ 37ኛው ደቂቃ ሀዲያዎች ከቀኝ መስመር ፍራኦል መንግስቱ ያሻገረለትን አብዱልሰመድ አሊ ሳይረጋጋ ቀርቶ ያልተጠቀመባት ኳስ ሌላኛው ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
ከእረፍት መልስ ምንም እንኳ መልካም የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ ብንመለከትም በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ውዝግቦች ጨዋታው እየተቆራረጠ እንዲደበዝዝ አድርጎታል። ከነዓን ማርክነህ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አጥብቦ ወደ ጎል የመታው እና በተከላካዮች ተደርቦ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣው ኳስ አዳማዎች ሁለተኛ ጎላቸውን እስካስቆጠሩበት ጊዜ ድረስ ብቸኛ የሁለተኛ አጋማሽ የጎል ዕድል ነበር። የሁለቱ የሀዲያ አጥቂዎች ቢስማርክ አፒያ እና ቢስማርክ ኦፖንግ ጥምረት ለአዳማ ተከላካዮች ፈታኝ ሆኖ ብንመለከትም ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አለመፍጠራቸው ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
73ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው የሀዲያ የመስመር አጥቂ ኢዩኤል ሳሙኤል ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ በግልፅ ተጎትቶ እያለ ኳሱን ወደ ጎል በመምታት ሙከራ በማድረጉ የዕለቱ ዳኛ ኳሱን ተጠቅመህበታል በማለት ፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጡ በዝምታ ማለፋቸው ተጫዋቾቹን እና ደጋፊዎችን ለሌላ ለተቃውሞ አስነስቷል። ብዙም ሳይቆይ ራሱ ኢዩኤል ሳሙኤል ይሁን እንደሻው ከሳጥን ውጭ ወደ ጎል የመታውን በተከላካዮች ሲደረብ ያገኘውን ነፃ ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረው ለነብሮቹ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
አዳማዎች በጫና ውስጥ ሆነው አዲስ ህንፃ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ቡድኑን በማረጋጋት የጨዋታውን መጠናቀቀ እየተጠባበቁ ባለበት ሰዓት ተቀይሮ የገባው ፉአድ ፈረጃ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት በመሄድ ለዳዋ ሆቴሳ አቀብሎት አጥቂው ሳጥን ውስጥ ተከላካይ በማለፍ በድጋሚ አቀብሎት ፉአድ ሁለተኛውን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በአዳማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ