የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 2-0 ሀዲያ ሆሳዕና

10ኛ ሳምንት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም አዳማ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2–0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኃላ የአሰልጣኞች አስተያየትን በከፊል አግኝተናል።

👉 “ይህ ቡድን ነገሮች ቢስተካከሉለት ኖሮ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የሚችል አቅም ነበረው” ም/አሰልጣኝ ደጉ ዱባም (አዳማ ከተማ)

የጨዋታ እንቅስቃሴ

ከድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ አስቀድሞም ቢሆን እንደ ቡድን ተሰባስበን ልምምድ መስራት አልቻልንም። እንደዛም ሆኖ ሜዳ ላይ ተጫዋቾቹ ባላቸው የመጫወት ፍላጎት እና ተነሳሽነት ምንም ነገር ማድረግ እንደሚችሉ በዛሬው ጨዋታ ተመልክተናል። ተጫዋቾቹ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነው ክለቡን በመውደድ እና ህዝቡን በማክበር ላደረጉት ነገር ሊመሰገኑ ይገባል።

የቡድኑ ችግር የፈጠረው ተፅእኖ

ምንም ጥያቄ የለውም ለተጫዋቾቹ ደሞዝ አለመከፈሉ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል። እስካሁን ወደ አስራ አምስት ቀናት እንደ ቡድን ተሰባስበን ልምምድ መስራት አልቻልንም። ቡድኑ ውስጥ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጀምሮ እስከ ተስፋኛ ወጣት ተጫዋቾች ጭምር የያዘ ነው። ይህ ቡድን ደሞዝ በአግባቡ ቢከፈለውና ነገሮች ቢስተካከሉለት ኖሮ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የሚችል አቅም ነበረው።

*አሰልጣኙ ይህን አስተያየት እየሰጡ ባለበት ወቅት ስታዲየም ውስጥ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት ም/አሰልጣኙ ደጉ ቃለ መጠየቁን ለማቋረጥ ሲገደዱ በማስከተል አስተያየታቸውን ሊሰጡ የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ አስተያየትን ለማካተት ሳንችል ቀርተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ