ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ ሲዳማን አሸንፎ ከመሪው ያለውን ልዩነት አጥብቧል

ትላንት የጀመረው 10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬም በ2ኛ ቀን መርሐ ግብር ሲቀጥል ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ በዐፄዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አዲስ አምርቶ ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ሦስት ተጫዋች ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በፍቅሩ ወዴሳ፣ ዮናታን ፍስሀ በግሩም አሰፋ እንዲሁም አበባየሁ ዮሐንስ በዮሴፍ ዮሐንስ ተተክተዋል። ባለሜዳዋቹ ፋሲል ከነማዎችም በተመሳሳይ በሽረ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ውስጥ ዓለምብርሀን ይግዛውን በያሬድ ባዬ እና ሀብታሙ ተከሰተን በኢዙ ኡዛካ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት የዛሬ ዓመት ጥር 15 ባህር ዳር ከ ፋሲል ከነማ ባደረጉት ጨዋታ ወደ ጎንደር ሲመለሱ በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ላጡት ደጋፊዎች መታሰቢያ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥር የበላይ የነበሩት ፋሲሎች በሲዳማ የሜዳ አጋማሽ በማመዘን ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ጨዋታው እንደተጀመረ አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻማውና ኢዙ ሞክሮ ዘደ ውጪ በወጣው ሙከራ አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል። ዐፃዎቹ በጥሩ አጀማመራቸው ቀጥለው ገና በ10ኛው ደቂቃም መሪ መሆን ችለዋል። ከሲዳማ ቡናዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ የተቋረጠውን ኳስ በፈጣን የመስመር ሽግግር ወደ ፊት በማምራት የመስመር ተከላካዩ ሰዒድ ሀሰን ያቀበለውን ሙጂብ ቃሲም ተቆጣጥሮ በሁለት ተጫዋቾች መሐል አልፎ በጥሩ አጨራረስ በቀኝ እግሩ አስቆጥሮ መሪ ሆኗል።

ባለሜዳዎቹ በመስመር በኩል ሾልኮ በመግባት ስጋት መፍጠራቸውን ቀጥለው በ13ኛው ደቂቃ አምሳሉ አሻምቶት በሁሉም ተከላካይ በማለፍ አጥቂዎች ሳይደርሱባት የቀረችው እንዲሁም ሽመክት አሻምቶ ሙጂብ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚጠቀሱ ሲሆን በሲዳማ በኩል ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት ባደረጉት ጥረት በ19ኛ ደቂቃ በግራ መስመር ከአዲስ ግደይ የተቀበለውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ሳማኬ መልሶታል።

ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት ያለመ ቅያሪን በማድረግ ሰንደይን ምትኩን በማስወጣት አበባየሁ ዮሐንስን ገና በጊዜ በመቀየር የመሐል ክፍሉን በማጠናከር ጫናውን መቀነስ ቢችሉም በመጀመርያው አጋማሽ በተደራጀ ሁኔታ ወደ ፊት መሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል። ባለሜዳዎቹ በተቃራኒው በ33ኛው ደቂቃ ሽመክት ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በሱራፌል አማካኝነት ወደ ግብ መተው ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል።

የመጀመሪያው ጨዋታ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ የሲዳማ ተጫዋቾች በግብ ክልላቸው ለመቀባበል ሲሞክሩ በፈጠሩት ስህተት ኢዙ አዙካ አግኝቶ ያመቻቸለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ኦሴ ማዊሊ ሞክሮ በተቃራኒው ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣበት ኳስ የፋሲልን የጎል ልዩነት ልታሰፋ የተቃረበች ነበረች።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ሁለተኛው አጋማሽም የጨዋታ የበላይነት የነበራቸው ፋሲሎች በፈጣን እንቅስቃሴ ገና በጊዜ ጎል ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ሲደርሱ በቀላሉ ኳሶችን ሲያመክኑ ተስተውሏል። በሙከራ ደረጃ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት በሁለት ተጫዋች መሐል ያሳለፍለትን ኳስ ሙጂብ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኙም ሙጂብ ወደ ግብ ልኳት ለጥቂት የቋሚው በኩል ሲወጣበት ሱራፌል ዳኛቸው በ61ኛው ደቂቃ በጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የወጣበት አጋጣሚ እጅግ አስቆጪ ነበር።

በመልሶ ማጥቃት በሚገኙ እድሎች ጎል ለማስቆጠር ጥረቶች ሲያደርጉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች አስቆጪ የሚባል ሙከራ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን በሀብታሙ ገዛኸኝ፣ ተስፉ ኤልያስ እንዲሁም አበባየሁ ዮሐንስ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉ ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል። ጨዋታውም በጅማሬው በተቆጠረችው ብቸኛ ፋሲል ከነማ አሸናፊ ሆኖ ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማዎች ድሉን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 18 በማሳደግ ሁለተኛ ላይ ሲቀመጡ ሲዳማ ቡና በ12 ነጥቦች ወደ 10ኛ ዝቅ ብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ