የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 1-1 ኢትዮጵያ ቡና

ወልዋሎ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞቹ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

👉 ” ተደጋጋሚ የመጨረስ ችግሮች እያየን ነው” ዮሐንስ ሳህሌ (ወልዋሎ)

ስለ ጨዋታው

ጥሩ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል። ብዙ ጥፋት ያልበዛበትና ለዳኞች የማያስቸግር ነበር። እኛ በብዛት ወደ ፊት መሄድ እነሱ ኳሱን ይዞ መጫወት ነበር። ሁለት የተለያየ የአጨዋወት ስልት ያላቸው ቡድኖች ማለት ነው።

በኛ በኩል በተደጋጋሚ ግዜ የመጨረስ ችግሮች እያየን ነው ። ችግሩ ዛሬ አንዱ ላይ ይሆናል ከዛ ሌላው ላይ ይሆናል። የተለያዩ ተጫዋቾች ናቸው ጎሎች የሚስቱት። አንዳንድ ደሞ የማይረቡ ስህተቶች እንሰራና ዋጋ እንከፍላለን። ወጣት የበዛበት ቡድን ሲሆን ስህተቶች ይበዛሉ። የማጥቃት ፍላጎታችን ፣ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል በመሄድ እና በሙከራዎች ማድረግ ጥሩ ነበርን።

ስለ ቡድኑ የወጥነት ችግር

ይሄ የሁሉም ቡድኖች ችግር ነው። አንደኛው በአስራ ስድስተኛው ይሸነፋል። አንደኛው በሌላኛው ይሸነፋል። ይሄ ለእግር ኳሱ ጥሩ ነው። አንዱ ዝም ብሎ አሸንፎ ከወጣ ደጋፊም አይመጣም። ሌላው አብዛኞቻችን በየዓመቱ አዲስ ቡድን ነው ምንገነባው። ስለዚህ ጊዜ የለም ወጥነትን ለመፍጠር። ከዐምናው ኬይታ ብቻ ነው ያስቀጠልነው። እኛ ሌሎቹን በዝግጅት ቀድመናቸው ስለነበር የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች አሸነፍን። ከዛ ሌላው ደሞ እየተሻሻለ እና እየተነቃቃ መጣ። ይሄን መጥላት አይገባም፤ ምክንያቱም ቢያንስ ከአንድ እስከ ዘጠነኛ ያለው በአንድ ቀን ጨዋታ ደረጃው የሚለዋወጥ ነው።

👉 “ቡና ላይ ለምን በተለየ መንገድ እንደሚታይ አልገባኝም” ካሣዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ወልዋሎ ከሚጣል ኳስ ዕድል መፍጠር ነበር የገቡት። እነዛ የሚወርዱ ኳሶች ተቆጣጥሮ ለመጫወት ነበር። የሚወርዱ ኳሶችም በአብዛኛው እነሱ ይዘው በድጋሚ በአየር ኳሶች ነው ጥቃት ለመፍጠር ያሰቡት። በአብዛኛው የዘጠና ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ ይሄን ይመስል ነበር።

ስለ ግብ ዕድሎች

በቂ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም። ያንን ለመፍጠር መጀመርያ ወልዋሎ ለማጥቃት በፈለገበት መንገድ መቆጣጠር ያስፈልጋል። እዛ ውስጥ ነው ብዙ ጊዜ የቆየነው። እሱን ተቆጣጥረን ነው የጎል ዕድል መፍጠር ያለብን። ይሄ ግን ግዜ ወስዶብናል። ያ ነገር ነው ብዙ የግብ ዕድል እንዳንፈጥር ያደረገን።

ስለ ታፈሰ ቅያሪ

መጀመርያ ጉዳት ነበረበት። በቅርብ ነው በህክምና ባለሞያዎች ወደ ጨዋታ እንዲመለስ የተወሰነበት። ከጉዳት መጥቶ ቀጥታ ቢገባ ተቀይሮ ቢገባ ብለን ነው ይህን የወሰንነው።

በመሐል ስለ ሚቆራረጡ ቅብብሎች

ቅድም እንዳልኩት ነው ምክንያቱ። እነሱ ከየትም አቅጣጫ ነው ኳስ የሚጥሉት። ያ የተጣለውን ኳስ ተከትለው የሚመጡ የነሱ ተጫዋቾች አሉ። ኳሱን በማውረድ ቅድም እንደጠቀስኩት ጫና ተቋቁመን መጫወት ነበረብን። ግን ተጫዋቾቻችን ከዛ ጫና መውጣት አልቻሉም።

ስለ ሜዳ ውጭ ጨዋታዎች

ጉዞ ለሁሉም ነው። ከአዲስ አበባ ወጥቶ ነጥብ ማግኘት ለሁሉም ቡድን አስቸጋሪ እንደነበር ነው የምሰማው። አሁን ቡና ላይ ለምን በተለየ መንገድ እንደሚታይ አልገባኝም። ለምን ቡና ላይ የተለየ ነገር እንደሚጠበቅ አልገባኝም። ሁሉም ቡድን ላይ እንደዛ ነገር ስላለ ማለቴ ነው። ከሜዳ ውጭ ነጥብ ጥለው የሚመለሱም እንደዚ የሚጠየቁ ከሆነም ጥያቄው የጋራ ነው እኔም መመለስ ይኖርብኛል።

አንድ ቡድን የሚጫወተው በሜዳው ነው ብለህ ለባለ ሜዳው አሳልፈህ የምትሰጠው ነገር አለ። ይህንን አስተሳሰብ ከኛ ተጫዋቾች ማስወገድ አለብን። ግን በተለየ መልኩ ቡና ላይ መታየት የለበትም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ