የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 1-3 ዩጋንዳ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በባህር ዳር ስታዲየም በዩጋንዳ አቻው 3-1 ከተሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።


👉 “በጨዋታው የታየው ልዩነት እነሱ ያገኙትን እድል በአግባቡ አልተጠቀሙም እኛ ደግሞ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅምን” አዩብ ካሊፋ – ዩጋንዳ

ስለ ጨዋታው እና ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ

በቅድሚያ ፈጣሪን አመሰግናለሁ። በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ። በሜዳህ እና ከሜዳህ ውጪ የምትጫወታቸው ጨዋታዎች ፍፁም የተለዩ ናቸው። እኛም ዛሬ መጠነኛ የታክቲክ ለውጦችን አድርገን ለጨዋታው ቀርበን ነበር። ነገር ግን ዋነኛ እቅዳችን የነበረው ጨዋታውን ማሸነፍ የሚል ነው። ወደ ሜዳ ስንገባ ለተጨዋቾቼ ኳሱን እንዲይዙ ነግሬያቸው ነበር። ግን የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ይህንን አልፈቀዱልንም።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን

ተጋጣሚያችን ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ በጣም ጥሩ ነበሩ። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ነበር። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው ተመልክቻቸዋለሁ። በጨዋታው የታየው ልዩነት እነሱ ያገኙትን እድል በአግባቡ አልተጠቀሙም እኛ ደግሞ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅመን ጎል አገባን። በዚህም ጨዋታውን አሸንፈን ወጣን። በአጠቃላይ ተጋጣሚያችን የአጨራረስ ችግር ነበረበት። እድለኛ የመሆን ነገር እንዳለ ሆኖ።


👉 “በረጃጅም ኳስ እኛ ላይ አደጋ ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል” ሳሙኤል አበራ – ኢትዮጵያ

ጨዋታው እንዴት ነበር

ጨዋታው እንደጠበቅነው አልነበረም። በዝግጅት ጊዜ ጨዋታውን እንዴት እናሸንፋለን የሚለው ላይ ስንሰራ ነበር። ነገር ግን የኳስ ነገር ሆኖ ሳይሳካልን ቀርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ብንጠቀም ኖሮ ጨዋታውን ልናሸንፍ እንችል ነበር። በአጠቃላይ እኛ ያገኘናቸውን አለመጠቀማችን እና እነሱ ያገኙትን መጠቀማቸው ዋጋ አስከፍሎናል።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተፈጠሩት ነገሮች

ዋና ሃሳባችን የነበረው ማጥቃት እና ጎል ማስቆጠር የሚል ነበር። ነገር ግን የግብ ጠባቂያችን እና የተከላካይ ክፍላችን የመናበብ ጉዳይ ዋና አስከፍሎናል። በተለይ ሁለተኛው ጎል የተቆጠረብን መንገድ በመናበብ ችግር በተፈጠረ ስህተት ነው። በአጠቃላይ ግን በሁለተኛው አጋማሽ የነበረን ጉጉት ከጨዋታው እንድንወጣ አድርጎናል። እነሱም ደግሞ በረጃጅም ኳስ እኛ ላይ አደጋ ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።

ተጨዋቾች የምትፈልገውን ተግብረዋል?

ተጨዋቾቻችን በመጀመሪያው አጋማሽ የምንፈልገውን ሲሰሩልን ነበር። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ የምንፈልገውን እና የምናስበውን አልነበረም ስንጫወት የነበረው። ይህ ደግሞ ከጫና የመጣ እንደሆነ እረዳለሁ። ተጨዋቾቼ ውጤቱን በጣም ይፈልጉት ስለነበር ጫና ውስጥ ገብተው ነበር። ከምንም በላይ ግን ጎል ሲገባብን የሂሳብ ስሌት ውስጥ ገብተን ስለነበረ በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ አልቻልንም።

ቀጣይ የቡድኑ እቅድ እና እጣ ፈንታ

ይህ ውጤት ለቡድናችን ትምህርት የሚሰጥ ነው። ከዚህ በኋላ የተሻለ ነገር ለመስራት እንጥራለን። በእርግጠኝነት ከፌደሬሽናችን ጋር በመነጋገር ለወደፊት ቡድኑን ለማጠናከር እንሞክራለን። በተለይ ከ17 ዓመት በታች ውድድር በሃገራችን ቢኖር የተሻሉ ነገሮችን ለማከናወን ይጠቅመናል። ውድድር በሌለበት ትንሽዬ ፍንጭ ማሳየታችን እንደውም ጥሩ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ