የአሰልጣኞች አስተያየት| ወልቂጤ ከተማ 1-0 ድሬዳዋ

በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማን በሜዳው ያስተናገደው ወልቂጤ በጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።


👉 “በሜዳችን እንደመጫወታችን ሶስት ነጥብ ለማሳካት ልጆቻንን ብዙ ጥረዋል” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ከብዙ ጨዋታ ነጥብ በኋላ ነው ማሸነፍ የቻልነው። ጨዋታውን በሜዳችን እንደመጫወታችን ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማሳካት ልጆቻንን ብዙ ጥረዋል። ይህን ውብ ደጋፊ ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝቶ ለማስደሰት ልጆቻን ያቅማቸውን ጥረዋል። ተጋጣሚያችን ይዞት የመጣውን አጨዋወት ሙሉ ለሙሉ እንዳይተግብር አድርገነው ነበር። በአጋጣሚ ወደፊት የሚጣሉ ኳሶችን ለመጠቀም ቢያስብም ይህ ነው የሚባል አደጋ አልፈጠሩም ነበር። ልጆቻንን ባስመዘገቡት ውጤት እጅጉን ደስተኛ ነኝ።

ከጠዋት ጀምሮ በከተማዋ የነበረው እንቅስቃሴ እጅግ አስደሳች ነበር። እንግዳውን ቡድን ከመቀበል አንስቶ በደጋፊው የተሰሙት ህብረ ዝማሬዎች እጅግ ውብ ነበሩ። ልጆቻንን ይህን ጨዋታ በማሽነፍ ሶስት ነጥብ ለደጋፊዎቻችን ለመስጠት ያቅማቸውን ጥረዋል። በቀጣይ ከደጋፊው ጋር በመሆን ወደፊት እንጓዛለን። ስለነበረው አደጋገፍ እና ለታየው ስፖርታዊ ጨዋነት በቡድኑ ስም አመሰግናለው።

👉 “በሜዳው ምክንያት ይዘን የመጣነውን የጨዋታ እቅድ ለመተግበር ከብዶናል።” ስምዖን ዓባይ (ድሬዳዋ ከተማ)

” በ90 ደቂቃ ጨዋታ ውስጥ ብዙ ነገሮች አሉ። ከዛ ውስጥ የኛን ቡድን አላማ እንቅስቃሴ ለመተግበር መቻል ነው። ነገር ግን እዚህ ሜዳ ላይ ለመተግበር ከባድ ነው። ሜዳው አመቺ አይደለም። ምክንያት ስትሰጥ መሸነፍህን ለመሸፈን ይመስላል። ቢሆንም ግን በሜዳው ምክንያት እኛ ይዘን የመጣነውን የጨዋታ እቅድ ለመተግበር ከብዶናል። ልጆቼ ለመተግበር የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል። ጨዋታውን በአጠቃላይ ውጤቱ አይገልፀውም። በረጃጅም ኳስ ነበር የሚጫወቱት። በአጋጣሚ የተሻገረ ኳስ ግብ አስቆጠሩ።

የኛ ጥረት ብቻ ጥቅም የለውም። የዛሬው ዳኝነት በጣም ጥሩ አልነበረም። ልጆቼ ያቅማቸውን በማድረጋቸው ኮርተንባቸዋል። ደጋፊው ጨዋ ደጋፊ ነው። ሙሉ ጨዋታ ቡድኑን ሲያበረታታ ነበር። ይህ አይነቱ ተግባር ሊበረታታ ይገባል።


© ሶከር ኢትዮጵያ