ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ድል አሳክቶ ከግርጌው ተላቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአስረኛ ሳምንት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ ከአምስት ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ 1-0 በመርታት ወሳኝ ሦስት ነጥቦች አሳክቷል፡፡

በዘጠነኛው ሳምንት ወደ ሐይቆቹ ተጉዘው ሽንፈት ያስተናገዱት ወልቂጤዎች ከመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸው ውስጥ በርካታ ተጫዋቾች በመለወጥ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። ግብ ጠባቂው ሳሆሆ ሜንሳህን ጨምሮ አቤኔዜር ኦቴ ፣ ኤፍሪም ዘካርያስ ፣ በረከት ጥጋቡ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ አባይነህ ፋኖ እና ጃኮ አረፋትን በማሳረፍ ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ አዳነ ግርማ ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ አሳሀሪ አልማሀዲ ፣ ፍፁም ተፈሪ ፣ ሳዲቅ ሲቾ እና አህመድ ሁሴን በተሰላፊነት አስገብተዋል፡፡ ድሬዎች በበኩላቸው በሜዳቸው አዳማን ካሸነፈው ስብስብስ ሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ በዚህም ያሬድ ዘውድነህ እና ያሬድ ታደሰን በማሳረፍ ዘሪሁን አንሼቦ እና በረከት ሳሙኤልን ተክተዋል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ቀዳዳን ፈልጎ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመድረስ ጫና መፍጠር የቻሉት ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያዎቹ 5 ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ በአህመድ ሁሴን አማካኝነት የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በጨዋታው ጥሩ የነበረው ጫላም በ14ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ለትሞ የወጣበት አጋጣሚ እጅጉን ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። በ23ኛው ደቂቃ ላይም ጫላ ተሺታ ሁለት ተጫዋቹችን በማለፍ ያቀበለውን ኳስ ሳዲቅ ሴቾ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ተረጋግቶ በመቆጣጠር ለቡድኑም ሆነ ለራሱ የመጀመሪያውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ሠራተኞቹ መሪነታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች በአህመድ ሁሴን፣ ጫላ ተሽታ፣ ሳዲቅ ሲቾ እና ይበልጣል ሽባባው አማካይነት መፍጠር ችለዋል። በተቃራኒው መሐል ላይ የተገደቡ የጨዋታ ሂደቶችን ያስመለክቱት ድሬዎች አልፎ አልፎ በረጅሙ ከሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲደርጉ የነበሩ ሲሆን ሙኅዲን ሙሣ እና ሬችሞንድ ኦዶንጎ አማካይነት የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

ከእረፍት መልስ ወልቂጤዎች የ3-5-2 ቅርፅ ባለው ቡድን ጨዋታቸውን ሲቀጥሉ ውጤቱንም ለማስጠበቅ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሙከራ አድርገዋል። በተቃራኒው ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅጉን ተሽለው የነበሩት ድሬዳዋዎች የተነቃቃ እንቅስቃሴን አስመልክተዋል፡፡ ድሬዎች ወደ ግብ ከደረሱባቸው አጋጣሚዎች መካከልም በ54ኛው ደቂቃ ተጋጣሚያቸው ሳጥን መስመር ላይ ኤልያስ ማሞ አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘበት ይጠቀሳል።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ከኋላ በቁጥር በዝተው ውጤቱን ማስጠበቅ የፈለጉት ወልቂጤዎች በመልሶ ማጥቃት እንዲሁም የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ለመጫወት ምርጫቸው ሲያደርጉ በሙከራ ረገድ ከዕረፍት መልስ ጫላ ተሽታ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ያደረጉት ከግብ ሙከራ ተጠቃሽ ናቸው። እንግዳው ቡድን ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ በእንቅስቃሴ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ወደ ተጋጣሚው አደገኛ ክልል አልፎ መግባት ተስኖት የነበር ሲሆን ከርቀት በሚመቱት ኳሶች አቻ ለመሆን ሞክሯል። በመጨረሻው ደቂቃ ላይም በግምት ከ18 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ሬችሞንድ ኦዶንጎ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ የግብ ጠባቂው ይድነቃቸው የግል ብቃት ታክሎበት ከግብነት ሊድን ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በወልቂጤዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ከመጨረሻ ደረጃው በመላቀቅ 14ኛ ላይ ሲቀመጥ ድሬዳዋ ከተማ ወደ 15ኛ ተንሸራቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ