የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ስለ ደጋፊዎች ተቃውሞ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል

በክረምቱ ሳይጠበቅ ፈረሰኞቹን የተረከቡት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ መንበራቸው እየተነቃነቀ ይመስላል። ከሰሞኑ ከደጋፊዎች ጫና ጋር በተያያዘ ለወትሮው ልምምድ ከሚሰሩበት የአዲስ አበባው የልምምድ ማዕከል ወደ ቢሾፍቱው ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ያቀኑት አሰልጣኙ አሁንም ቢሆን በማሸነፍ ውስጥ እፎይታ ሊያገኙ አልቻሉም።

በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ ምንም እንኳን በጠባብ ውጤት ቢያሸንፍም አሰልጣኙ ከደጋፊዎች እንዲሁም ከገዛ ተጫዋቾቻቸው ተቃውሞ ሲገጥማቸው ተስተውሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኙ በደጋፊዎች ተቃውሞ ላይ ያላቸውን ሀሳብ በሚከተለው መልኩ አጋርተዋል።

” ይህ የተለመደ ነው፤ የትኛውም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመጣ አሰልጣኝ ጫናዎች አሉበት። ምክንያቱም ደጋፊዎቹ ቡድኑ ሁሌም ጨዋታዎች እንዲያሸንፍና ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ነገርግን ደጋፊው መረዳት የሚኖርበት ዋንጫ ለማንሳት ሁሌም መንገዶች ቀላል አይሆኑም። እያሸነፍንም ቢሆን በጨዋታዎች ላይ ደጋፊዎች ከቡድኑ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን እየፈለጉ ደስተኛ ባይሆኑ እኔ ብዙ ግድ አይሰጠኝም። አሁን ላይ ሁሉም በክለቡ ዙርያ ያሉ አካላት ደስተኛ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም ከመሪው መቐለ በሁለት ነጥቦች ርቀን 17 ነጥብ መያዝ ችለናል። ዋናው ነገር ጎሎችን እያስቆጠርን ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻላችን ነው።”

አሰልጣኙ በተጨማሪም ሰሞኑን ስማቸው ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ማመልከቻ ጋር ስለመያያዙ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። “ይሄ በጣም የቆየ ነገር ነው። ነገሩ የሆነው ዛምቢያውን ቢውልድ ኮን ክለብ በለቀቅኩ ጊዜ የተፈጠረ ነገር ነው። ይህ ማለት ደግሞ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመምጣቴ በፊት የሆነ ነገር ነው። አሁን ላይ እዚህ ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ። እዚህ ከመምጣቴ በፊት ስለሆነ ነገር አሁን ላይ መነሳቱ አግባብ አይደለም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ